ፕሬዝዳንት ትራምፕ ሰሜን ኮሪያን ሽብርተኝነትን ትደግፋለች አሉ

ህዳር 12፣2010

አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ፈረጀቻት፡፡

አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ውሳኔ በኮሪያ ልሳነ ምድር የነገሰውን ውጥረት ከድጡ ወደ ማጡ እንዳያደርገው ተሰግቷል፡፡

ይህ የአሜሪካ ውሳኔ የተላለፈውም ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ እና የሚሳዮል ሙከራ መርዓ -ግብሯን ስላላቆመች እንዲሁም በአለም አቀፍ ደረጃ በሽብር ተግባር ተሳታፊ ነች በሚል ነው፡፡

ይሁን እንጂ አዲሱ የአሜሪካ ውሳኔ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ እና የሚሳዮል ሙከራ መርዓ -ግብሯን እንድታቆም የሚደረገውን የዲፕሎማሲ ጥረት ያሰናክለዋል ተብሎ ተፈርቷል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በካቢኔ ስብሰባቸው እንዳስታወቁት ሰሜን ኮሪያ በመንግስታቱ ድርጅት የተከለከለችውን የጦር መሳሪያ ሙከራ መርዓ ግብሯን ካላቆመች አዲሱ የሀገራቸው እርምጃ ተጨማሪ ከባድ ማዕቀቦች ለመጣል በር ይከፍታል፡፡

አዲሱን የአሜሪካ እርምጃን ተከትሎም ሰሜን ኮሪያ ተጨማሪ የኒውክሊየርና የሚሳዮል ሙከራ ልታደርግ ትችላለች ተብሎ ተገምቷል፡፡

ሰሜን ኮሪያን በአለም አቀፍ ደረጃ በተደጋጋሚ በሽብር ድርጊት ተሳታፊ ናቸው ተብለው ከተፈረጁ እንደ ሶሪያ፣ ሱዳንና ኢራን ሀገሮች ዝርዝር ውስጥ ነው የተካተተችው፡፡

አሜሪካ እ.ኤ.አ ከ2008 በፊት ሰሜን ኮሪያን በአለም አቀፍ ደረጃ ሽብርተኝነትን ከሚደግፉ ሀገሮች ዝርዝር ውስጥ ፈርጃት ነበር፡፡

ሆኖም ከዘጠኝ ዓመት በፊት የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆርጅ ቡሽ የሰሜን ኮሪያን የኒውክለር መርዓን ለማቆም የሚካሄደውን ድርድር የሰመረ ለማድረግ ሀገሪቱን ከአለም አቀፍ ሽብርተኝነት ማዕደር ውስጥ ሰርዘዋት ነበር፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ