በሚዛን በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ እምነት እንደሌላቸው ተጠቃሚዎች አስታወቁ

ህዳር 12፡2010

በንግድ ልውውጥ ወቅት በሚዛን በሚሰጡ አገልግሎቶች ላይ እምነት እንደሌላቸው ተጠቃሚዎችአስታወቁ።

ኢቢሲ ያነጋገራቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደገለፁት በስጋ ቤቶች፣ በአትክልት ቤቶችና በችርቻሮ ሱቆች ያሉ ሚዛኖች ትክክለኛ ልኬት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ ገለፃ በመንገድ ላይ የሚሸጡ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በሚዛን መግዛት አስተማማኝ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡

አዲስ አበባ የሚገዛው አንድ ኪሎ ስጋ ከአዲስ አበባ ውጭ በሆኑ ስጋ ቤቶች ከሚገዛው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለውም ተጠቃሚዎቹ ተሞክሮአቸውን አካፍለውናል፡፡

ሚዛኑን ለራሳቸው ብቻ እንደሚታይ አድርጎ ማስቀመጥ፣ ሚዛኑ ትክክለኛውን ልኬት እንዳያሳይ በመጠምዘዝ ማስተካከል እና ትክክለኛ የሚዛን ማነፃፀሪያ ድንጋይ ያለመጠቀም በከተማዋ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ነዋሪዎቹ ትክክለኛ ባልሆኑ ሚዛኖች እየተታለሉ እንደሚገኙ በመግለፅ የሚመለከተው የመንግስት አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ ከብሄራዊ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ በመሆን በከተማዋ ጤናማ ግብይት እንዲኖር እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ንግድ ቢሮው በመደበኛነት የሚዛኖችን ትክክለኛነትን እንደሚቆጣጠርና ህጉን ተላልፈው በሚገኙ ነጋዴዎች ላይም እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል፡፡

በቅርቡ ደግሞ ወጥ የዲጅታል ሚዛን አገልግሎት ወደ ስራ እንደሚገባም በንግድ ቢሮ የንግድ ክትትልና ቁጥጥር የስራ ሂደት መሪ አቶ ካሳሁን በየነ ተናግረዋል፡፡

አዲሱ ሚዛን በቀላሉ በእጅ ተጠምዝዞ ወደ ኋላ ለመመለስ የማይቻልና በቢሮው ባለሞያዎች ብቻ በሚታወቅ የሚስጥር ቃል የሚቆለፍ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ