ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ባስመዘገበችው የላቀ ውጤት አለም አቀፍ ሽልማት አገኘች

ህዳር 12፡2010

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2017 ኢንቨስትመንትን በመሳብ ባስመዘገበችው የላቀ ውጤት አለም አቀፍ ተሸላሚ ሆነች።

የተባበሩት መንግስታት በየዓመቱ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር የተጣጣመ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ውጤት ላስመዘገቡ ሃገራት የሚሸልመውን ሽልማት ኢትዮጵያ እኤአ በ2017 ባስመዘገበችው የላቀ አፈፃጸም አለማቀፍ ተሸላሚ ሆናለች።

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ የተመራ የልዑካን ቡድን የመንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ኮንፈረንስ ላይ ተገኝቶ ሽልማቱን ተቀብሏል።

ኮሚሽኑን ለሽልማት ያበቃው ጥራት ያለው ኢንቨስትመንት በመሳብና ድጋፍ በመስጠት ባከናወናቸው ስራዎች እንዲሁም ለዘላቂ የልማት ግቦች አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በተሳካ ሁኔታ ማከናወን በመቻሉ መሆኑ ተገልጿል።

አገሪቱ የነደፈችውን የአረንጓዴ የኢንዱስትሪ የልማት ስትራቴጂ ከብክለት ነፃ ተደርገው በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተመረጡ ኢንቨስተሮችን መሳብ መቻሉና ለሌሎችም መሰል ሃገራት ምሳሌ መሆን የሚያስችል ስራ መሰራቱ ለሽልማት እንዳበቃው ተጠቅሷል።

በቅርቡም የዓለም ባንክ ውጤታማ የፓሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎችን በመተግበር ኢንቨስትመንትን በመሳብ ሃገሪቱ በዓመቱ ባስመዘገበችው አመርቂ ውጤት የኮከብ ፈፃሚ ደረጃ (2017 Star Reformer Award) ለኢትዮጵያ መንግስት እንደተበረከተለት የሚታወስ ነው።

ምንጭ፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን