የአፍሪካ ህብረት በሊቢያ በሚገኙ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እንዳሳሰበው አስታወቀ

ህዳር 12፡2010

የአፍሪካ ህብረት በሊቢያ በሚገኙ ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እንዳሳሰበው አስታወቀ።

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ሊቢያ በባርነት ግዞት ውስጥ በሚገኙ የአፍሪካ ስደተኞች ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙትን የህብረቱ ተጠሪ አምባሳደር ዶ/ር ሰዲህ ኢልዋይሪን አነጋግረዋል፡፡

ሊቀ-መንበሩ ህብረቱ በአፍሪካውያን ስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ እንደሚያሳስበውና ይህ ጉዳይ ተአማኒ በሆነ አካል ተጠንቶ የሊቢያ መንግስት ወንጀለኞች ለህግ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ  አሳስበዋል፡፡

የሊቢያ መንግስት በስደተኞች ላይ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጥናት ተልእኮ ከተሰጠው የአፍሪካ ህብረት ቡድን ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

አምባሳደሩም በበኩላቸው የሊቢያ መንግስት እንደዚህ ያለውን ተግባር እንደሚያወግዝና በድርጊቱ እጃቸው ያለበትን ሰዎች ለህግ ለማቅረብ ከህብረቱ ጋር በትብብር እንደሚሰራ ለኮሚሽኑ ሊቀመንበር ገልፀውላቸዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞን ጉዳይ የሚያጠና እና በአገሪቱ የሚገኙ ስደተኞችን አያያዝ እንዲሻሻል ከሊቢያ መንግስት ጋር የሚሰራ የልኡካን ቡድን በቅርቡ ወደ ስፍራው እንደሚያቀናም ተገልጿል፡፡

ምንጭ፡- የአፍሪካ ህብረት