የኬንያ ዳግም ምርጫ ውጤት የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አጸደቀ

ህዳር 11፣2010

የኬንያ አጠቃላይ ዳግም ምርጫ ውጤት የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡    

ባለፈው ወር በኬንያ ዳግም አጠቃላይ ምርጫ ተካሄዶ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ኬንያታ ማሸነፋቸው የሚያበስረውን ውጤት ያፀናው በምርጫው ውጤት ላይ ቅሬታ ቀርቦ ምርመራ ካደረገ በሃላ ነው ተብሏል፡፡

በዚህም መሰረት በፍርድ ቤቱ የተሰየሙት ስድስት ዳኞች በሁለት የህግ አቤቱታዎች ላይ ምርመራ ካደረጉ በሃላ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያሸነፉበትን ውጤት ህጋዊ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የፕሬዝዳንት ኬንያታ ተቀናቃኝ የሆኑት ነገር ግን በዳግም ምርጫው ያልተሳተፉት ራይላ ኦዲንጋ በበኩላቸው የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በፖለቲካ ተጽእኖ የተላለፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምርጫውን ተከትሎ የሚመሰረተው መንግስትም ህገወጥ በመሆኑ እውቅና አንሰጠውም ብለዋል፡፡

የአሁኑ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ውሳኔ የምርጫው አሸናፊ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በሚቀጥለው ሳምንት ለሚፈጽሙት  ቃለመሀላ  ምቹ መደላድል የፈጠረ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ምንጭ፦ ሮይተርስ