ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር ገቢሳ እጄታ ለምርጥ ዘር ልማት 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አገኙ

ህዳር 11፣2010

ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ፕሮፌሰር ገቢሳ እጄታ በግብርና ምርጥ ዘር ልማት ለሚያደርጉት ምርምር  አምስት ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ አገኙ።

በአሜሪካ የፑርዱ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ገቢሳ እጄታ ድጋፉን ያገኙት  ‹‹ቢልና መሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን›› ከሚባል ግብረሰናይ ድርጅት ነው።

በቢልና መሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የተሰጠው ድጋፍ ተመራማሪው አረም መቋቋም የሚችል የተዳቀለ ምርጥ ዘር እንዲያለሙ ለማስቻል ነው ተብሏል፡፡

ድጋፉ በተለይ ለታዳጊ ሀገሮች ግብርና ጠቃሚ እንደሆነ ፕሮፊሰር ገቢሳ ኢጀታ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ተመራማሪው ድርቅንና አረምን መቋቋም የሚችል ድቃይ የማሽላ ምርጥ ዘር ማግኘታቸው ይነገራል፡፡

አሁን ደግሞ ፕሮፊሰሩ ከስራ ባልደረቦቻቸ ጋር በመሆን የማሽላ ሰብልን የሚያጠቃ የአረም ዘረመልን ለማወቅ የሚያስችል ምርምር ለማስፋት እየሰሩ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡ 

ፕሮፊሰር ገቢሳ ኢጀታ በዘርፉ በሰሩት ስራ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ለሚገኙ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካዊያን የዕለት ጎርሳቸውን እንዲያገኙ በማድረጋቸው ተመስግነዋል፡፡

ለአብነትም ፕሮፊሰሩ ለ15 ዓመታት ያህል ምርጥ ዘር ለማግኘት ላደረጉት ምርምር የ2009 የአለም ምግብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ምንጭ፦ ዘ ሪፐፕሊክ ድረ-ገጽ