ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸዋል

ህዳር 11፣2010

ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ ፓርቲያቸው ዛኑ_ፒኤፍ ከፓርቲ መሪነታቸው በማንሳት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸውን እንዲለቁ እስከ ዛሬ 7 ሰዓት ቀነ ገደብ አስቀምጦላቸዋል፡፡

የስልጣን መልቀቅ ሂደቱ ግን ማክሰኞ ሕዳር 12/2010 ዓ.ም ፓርላማው እንደተሰበሰበ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል᎓᎓

ሮበርት ሙጋቤ ከፕሬዝዳንትነታቸው በራሳቸው ፍቃድ እንዲወርዱ ጫና ቢደረግባቸውም ትናንት በሰጡት መግለጫ ስልጣን እንደማይለቁ አስታውቀዋል።

ፓርቲው ግን  በሙጋቤ ምትክ ከሁለት ሳምንታት በፊት በፕሬዝዳንቱ የተባረሩትን የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋን የፓርቲው መሪ አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡ ቀዳማዊት እመቤት ግሬስ ሙጋቤን ደግሞ ከአባልነት አባሯል፡፡

የዚምባቡዌ ቀውስ የጀመረው ከሁለት ሳምንት በፊት የ93 አመቱ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ  ምክትላቸውን ከስልጣን በማባረራቸው ሲሆን ይህም በአንዳንድ የጦር አዛዦች ዘንድ ፕሬዝዳንቱ ባለቤታቸውን ቀጣይ ፕሬዚዳንት አድርገው ሊሾሙ ነው የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ ነው ተብሏል᎓᎓

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዚምባቡዌ በተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች እየታመሰች ትገኛለች ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው᎓᎓