ቋሚ ኮሚቴው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የስራ አፈፃፀም ሪፖርትን ገምግሟል

ህዳር 04፣2010

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት የ2ዐ1ዐ በጀት አመት የ1ኛ አመት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስትር አቶ ታገሰ ጫፎ የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን በፌደራልና በክልል ደረጃ በተሻለ አፈፃፀም እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሀገር ደረጃ ከ15ሺ በላይ ስራዎች ደረጃ እንደወጣላቸውም ገልፀዋል፡፡ ሚኒስትሩ አክለውም ከመልካም አስተዳደር የፋይናንስ ኢኮኖሚ የአስተዳደርና ፍትህ እንዲሁም የማህበራዊ ዘርፍ ተቋማትን በተለየ አግባብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የተሻለ አፈጻጸም እንዲያስመዘግቡ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆኑትን የካይዘን ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሪፖርትን የገመገመ ሲሆን ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው ግብረ መልስ የተቋም ስራዎችን በጥራትና ውጤታማነት ለመፈፀም የሚያስችሉ የለውጥ መሳሪያዎችን፣ የካይዘን አመራር ፍልስፍና፣ የዜጎች የስምምነት ሰነድ በመከለስ መስራት መጀመሩን፣ የህዝብ እርካታ ደረጃ ለማወቅ የሚረዳ ጥናት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መጀመሩን፣ በጥንካሬ ተመልክቷቸዋል፡፡

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱን የውስጥና የውጭ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በእቅዱ መጠን ያለመፍታትና የስራ ምዘናና ደረጃ አወሳሰን አለመጠናቀቁንና በጋምቤላ ክልል ተግባሩ አለመጀመሩን ቋሚ ኮሚቴው በእጥረት ተመልክቷቸዋል ሲል የዘገበው ተስፉ ወ/ገብርኤል ነው፡፡