በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የደህንነት ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

ህዳር 3፣2010

በሶማሊያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የደህንነት ስራውን ማጠናከር እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት ገለጸ፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል አሚሶም በሶማሊያ የፀጥታ ጉዳይ ላይ በሞቃዲሾ  መክረዋል፡፡

በምክክሩ የሶማሊያ ሚንስትሮች፣ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባለት ተሳትፈውበታል፡፡

በሶማሊያ አሸባሪዎች የሰላምና ደህንነት ስጋት መሆናቸውን ቀጥለዋል ያሉት በሶማሊያ የተባበሩት መንግሰታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ልዩ ተወካይ ማይክል ኪቲንግ ዋናው ጉዳይ በሀገሪቱ እንዴት መረጋጋት እናምጣና የተገኙ ውጤቶችን እናስቀጥል የሚለው መሆን አለበት ብለዋል፡፡

ልዩ ተወካዩ በሶማሊያ የፖለቲካ ምህዳሩን መጠበቅ ሀገሪቱን የመገንባት ስራውን ለማስቀጠል፣ ሰላምን ለመገንባትና የማህበራዊ ኢኮኖሚውን ችግር ለመቅረፍ እንደሚያግዝም ገልፀዋል፡፡

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ልዩ ተወካይ ፍራንሲስኮ ማድሪያም በሶማሊያ የደህንነት ችግሮችን ለመቅረፍ ጠንካራ ጥረት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሶማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሃሰን አሊ ካይር በሶማሊያ ደህንነትን ለማረጋገጥ ሁሉን አቀፍ መፍትሄ ወሳኝ መሆኑን በምክክሩ ላይ ተናግረዋል፡፡

ለሶማሊያ ደህንነት አሸባሪዎች ላይ ብቻ ጥቃት ማድረስ በቂ አለመሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሙስናን መዋጋት፣ መልካም አስተዳደር ማስፈንና መሰል ጉዳዮች ለሶማሊያ ሰላም ወሳኝ መሆናቸውን መገንዘብ አለብን ማለታቸውን ዢንዋ ዘግቧል፡፡