የኢጋድ አባል ሃገራት በመሬት አስተዳደር ላይ የሚያደርጉትን ውይይት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኢትዮጵያ ጥሪ አቀረበች

ጥቅምት 30 ፤2010

በመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት እንዲቻል የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት /ኢጋድ/ አባል ሃገራት የሚያደርጉትን ውይይት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ኢትዮጵያ ጥሪ አቅርባለች፡፡

ኢጋድ በጉዳዩ ዙሪያ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ጉባኤውን በጀመረበት ወቅት የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር ድኤታ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ እንደገለጹት አፍሪካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት መሰረቱን ያደረገው በመሬት ላይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና በአግባቡ መመራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

አባል ሃገራት የሚያደርጉት የጋራ ምክክር የአፍሪካ ህብረት የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር አዋጅን ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳ በመሆኑ ለኢጋድም ሆነ ለልማት አጋሮች ውጤታማነት እጅጉን ይረዳል ነው ያሉት፡፡

ይህ ጅማሮው እንጂ የመጨረሻው እንዳልሆነ የገለጹት ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ፤ አባል ሃገራት በመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ ያካበቱትን ልምድ ማካፈል እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ኢጋድ በመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ ይህ መሰል ውይይት ሲያደርግ የመጀመሪያው እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ምንጭ፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር