በሊቢያ አቅራቢያ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ሰምጣ 5 ሰዎች ሞቱ

ጥቅምት 28፣2010

በሊቢያ አቅራቢያ ስደተኞችን የጫነች ጀልባ ሰምጣ 5 ሰዎች ሞተው ፣ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ስደተኞች የደረሱበት አልታወቀም፡፡

የሊቢያ የድንበር ጠባቂዎችና የሰብዓዊ ድርጅቶች እንዳስታወቁት በምዕራባዊ ሊቢያ ጠረፍ አቅራቢያ ነው ስደተኞች የጫነችው ጀልባ የመስመጥ አደጋ የገጠማት፡፡

ጀልባዋ 140 ሰዎችን ጭና በሜድትራኒያን ባህር ላይ ወደ አውሮፓ ስታቀና እንደነበር ተመልክቷል፡፡

የሊቢያ የድንበር ጠባቂዎችና ሲዎች የተሰኘ የጀርመን በጎ አድራጎት ድርጅት በድምሩ የ103 ሰዎችን ህይወት ማትረፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ቀሪዎቹ ግን የደረሱበት አልታወቀም፡፡

በህይወት የተረፉት ደግሞ ከምዕራብ አፍሪካ ከአገራት በተለይም ከናይጀሪያና ሴኔጋል የተሰደዱ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

ሊቢያ የስደተኞች የአውሮፓ ዋነኛ መግቢያ ስትሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ህገ ወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች ስደተኞችን ይዘው በመጓዝ በመሀል የባህር አካል ላይ እየጣሉ በመገኘታቸውና የአውሮፓ የድንበር ቁጥጥሩ እየጠነከረ በመምጣቱ  የስደቱ መጠን ቀንሶ እንደነበር የሲጂቲኤን ዘገባ አመልክቷል፡፡