የጤና መድህንና የደም ባንክ አገልግሎት ኤጄንሲዎች ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸው ተመለከተ

ጥቅምት 25፤2010

የጤና መድህንና የደም ባንክ አገልግሎት ኤጄንሲዎች አገልግሎት አሰጣጣቸውን አስመልክቶ ለሕብረተሰቡ ግንዛቤ መስጠት እንዳለባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማሕበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የሁለቱን ተቋማት የ2010 በጀት አመት እቅድ ገምግሟል።

የጤና መድህን ኤጄንሲ በክልሎች የማሕብረሰብ የጤና መድህን ላይ የተሻለ ስራ ማከናወኑን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ አንስቷል።

ነገር ግን የጤና መድህን ማስተባበሪያ የሕግ ማእቀፍ አለመኖር፣ የአባላት ክፍያ አፈጻጸምና የኦዲት ስርዓት አለመጠናከር በድክመት ታይቷል።

ብሔራዊ የደም ባንክ የደም ለጋሽ አካላት ቁጥርን ከሰባት ሺህ ወደ አስር ሺህ ማሳደጉ፣ የደም ባንኮች ቁጥሮችን ለመጨመር መስራቱና የደም ለጋሽ ክልሎችን ወደ መቶ ለማድረስ መስራቱን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።

የጤና መድህንና ብሔራዊ የደም ባንክ ኤጄንሲዎች ያላቸው ዓላማና ተግባር ለዜጎች በቂ ግንዛቤ አለመፈጠሩ በከተማ አከባቢ የጤና መድህን የስራ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ፣ በአንዳንድ ክልሎች ከጤና መድህን በወቅቱና በአግባቡ ገንዘብ አለመሰብሰብ፣ በጤና ተቋማት ከጤና መድህን ተጠቃሚዎች ይልቅ በገንዘብ ህክምና ለሚያገኙ ቅድሚያ የመስጠት አዝማሚያ በቋሚ ኮሚቴው ድክመት ነው ተብሏል።

ኤጄንሲዎቹ ከመገናኛ ብዙሀን፣ ከጤና ተቋማትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ እንዲሰሩ እንደዚሁም ደግሞ ተሞክሮዎችን በመውሰድ እንዲተገበሩ ነው ቋሚ ኮሚቴው ያሳሰበው።

ቋሚ ኮሚቴው ከጤና መድህን የሚሰበሰበው ገንዘብ የአሰራር ስርዓቱ ሊጠብቅ እንደሚገባ ማሳሰቡን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተሮች ያደረሰን መረጃ አመልክቷል።