ናይጄሪያ የኒውክለር የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ልትገነባ ነው

ጥቅምት 22፣2010

ናይጄሪያ የገጠማትን የኤሌክትሪክ ኃይል ቀውስ የሚፈታ የኒውክለር  ሀይል ማመንጫ ለመገንባት የሚያስችላትን ስምምነት ከሩሲያ ጋር ተፈራርማለች፡፡

አገሪቱ ያጋጠማትን ከፍተኛ የሀይል እጥረት ይፈታል የተባለለት የኒውክሌር ፕሮግራሟ እስከ 20 ቢሊዮን ዶላር ሊፈጅ እንደሚችልም ተጠቁሟል፡፡

የሩሲያው ሮሳቶም ኩባንያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከናይጀሪያ ጋር መንግስት ጋር ሲደራደር ከቆየ በኃላ  የኒውክለር ኃይል ማመንጫውን ለመገንባት የሚያስችለውን ስምምነት ፈፅሟል፡፡

ሮሳቶም ከናይጄሪያ የአቶሚክ ኃይል ኮሚሽን  ጋር ስምምነቱን የፈረመው በቀጣይ 2 አመታት ውስጥ ወደ ተግባር ለመግባት ነው፡፡

የአሁኑ ስምምነት እ.ኤ.አ በ2009 በናይጄሪያና በሩሲያ መካከል በኒውክለር  ላይ በትብብር ለመስራት የፈፀሙት ስምምነት አካል ነው፡፡

የሩሲያው ድርጅት ተመሳሳይ ስምምነቶችን ከጋና እና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ለመፈፀም በድርድር ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

በ2014 በወጣው የአለም ባንክ መረጃ መሰረት የናይጄሪያ 40 በመቶ የሚሆነው ነዋሪ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት አያገኝም፡፡

ከ186 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ያሏት ናይጄሪያ በአፍሪካ ከፍተኛ የነዳጅ ሀብት ካላቸው አገራት አንዷ ብትሆንም በሙስና ምክንያት ለዜጎቿ ጠብ የሚል ነገር የሰራች አገር አልሆነችም፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ