አፍሪካ ህብረት እና ተ.መ.ድ በኬንያ ስላም እንዲሰፍን ጥሪ አቀረቡ

ጥቅምት 13፣2010

ዳግም በሚካሄደው የኬንያ ምርጫ ዋናው ተቃዋሚ ፓርቲ በምርጫው እንደማይሳተፍ መግለጹን ተከትሎ ያለው ውጥረት እንዲረግብ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ አስተላለፉ፡፡

ምርጫው በመጪው ሃሙስ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዟል፡፡

የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡህሩ ኬኒያታ ለምርጫው እየተዘጋጁ ቢሆንም ተቃናቃኛቸው ራይላ ኦዲንጋ ደግሞ በምርጫ ኮሚሽኑ እምነት የለኝም  በማለት፣ ደጋፊዎቻቸው በምርጫው እንዳይሳተፉ ጥሪ እያቀረቡ ነው፡፡

በመሆኑም ብሔርን መሰረት አድርጎ በተመሰረተው የሁለቱ ተቃናቃች ፓርቲዎች ውጥረቱ ነግሷል፡፡

ለዚህም ነው የአፍሪካ ህብረት ዋና ፀሓፊ ሙሳ ፋኪ ማሀማት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ ያቀረቡት፡፡

የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን ሰራተኞችም ከወዲሁ በስጋት ውስጥ ነን ማለታቸው ውጥረቱን ያሳያል ተብሏል፡፡

የዓለም መንግስታትም ኬኒያውያን ለሰላም እንዲሰሩ ጥሪ እያቀረቡ ነው፡፡

ከወር በፊት የተካሄደው የኬንያ ምርጫ በኡሩ ኬንያታ አሸናፊነት የተጠናቀቀ ቢሆንም ውጤቱ ራይላ ኦዲጋ የሚመሩት የተቃዋሚ ፓርቲ ክስ አቅርቦ በፍርድ ቤት ውድቅ መሆኑ ይታወሳል፡፡

በምርጫው ተቃዋሚ ፓርቲ የማይሳተፍ ከሆነ ኡሁሩ ኬንያታ በቀጥታ ስልጣኑን እንዲይዙ የሚያስችል ህግ የሀገሪቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት ማፅደቁ ይታወሳል፡፡ዘገባው የአሶሴትድ ፕሬስ ነው፡፡