አፍሪካ ራሷን መመገብ እስከምትችል እረፍት የለኝም:- የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕ/ት

ጥቅምት 11፣2010

የአለም ምግብ ሽልማት አሸናፊው የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዶክተር አኪኒዋሚ አዲሲና አፍሪካ በምግብ ራሷ እስከምትችል ድረስ እረፍት እንደማይኖራቸው ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የአውሮፓውያኑ 2017 የአለም ምግብ ሽልማትን አሸንፈው ሽልማታቸው ሲቀበሉ ነው።

ፕሬዝዳንቱ በናይጄሪያ የግብርና ሚኒስትር እያሉ ግብርናውን ለማዘመን ለሰሩት ሥራ ነው ሽልማቱ የተበረከተላቸው፡፡

የ57 አመቱ ዶክተር አኪንዉሚ አዲሲና በሽልማቱ ያገኙትን 250ሺ ዶላር በግብርና ለሚተዳደሩ አፍሪካያን ወጣቶች እንደሚያውሉትም ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ በአነስተኛ ማሳ የሚተዳደሩ አርሶ አደሮች ልጆቻቸውን መግበው ወደ ትምህርት ቤት መላክ የሚችሉበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለዋል።

አፍሪካ በየአመቱ በ35 ቢሊዮን ዶላር ምግብ ከውጭ ታስገባለች። አሀዙ በአውሮፓውያኑ 2030 በአማካይ 110 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል።

አፍሪካ ሶስት መቶ ሚሊዮን ዜጎቿ ለረሀብ ተዳርገዋል። 54 ሚሊዮን ህጻናትም ለአካላዊ እድገታቸው የሚበቃ በቂ ምግብ አያገኙም ተብሏል።

645 ሚሊዮን አፍሪካውያን የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት እንደማያገኙ የገለጹት ዶክተር አዲሲና በአህጉሩ ትርጉም ያለው የኤሌክትሪክ፣ መንገድ፣ የባቡርና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

አፍሪካ በጨለማ ማደግ አትችልም ያሉት ዶክተሩ የግብርና ምርቷን እሴት እየጨመረች ወደ ውጭ ለመላክም ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት   ያስፈልጋታል ብለዋል።