በብክለት የሚከሰተው ጉዳት በታዳጊ አገራት ላይ እጅጉን የበረታ ነው ፦ ጥናት

ጥቅምት 10፤2010

በአለም በአካባቢያዊ ብክለት ሳቢያ የሚከሰት ሞት በአመዛኙ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሀገሮች ክፉኛ እየጎዳ እንደሚገኝ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

በዚህም ከስድስት የሰዎች ሞት ውስጥ አንዱ ከብክለት ጋር በተያያዘ  የሚከሰት መሆኑን ጥናቱን ያካሄዱት  በኒውዮርክ የሚገኙ ተመራማሪዎች ተናግረዋል፡፡

ሶማሊያና ባንግላዴሽ በችግሩ በእጅጉ ክፉኛ የተጠቁ አገሮች መሆናቸው ተመልክቷል፡፡

በአንፃሩ ስዊዲንና ብሩኒ ከብክለት ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሞት በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝባቸው አገሮች እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የአካባቢ ብክለት ከሚያስከትሉ መንስኤዎች መካከል የአየር ብክለት ከፍተኛ የሞት መጠን እንዲኖር በማድረግ ቀዳሚ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

አብዛኛውን ከብክለት ጋር የሚያያዙ ህልፈቶች የሚከሰቱትም ተላላፊ ባልሆኑ እንደ ልብ ህመም፣ ሳንባ ካንሰርና የአንጎል ደም መፍሰስ/ስትሮክ/ በሽታዎች እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

በአለም በብክለት ከሚከሰት ሞት መካከል የአየር ብክለት ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስድ ሲሆን የ6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሞት መከሰት ምክንያት ነው የሚባለው፡፡

የውሃ ብክለት የ1 ነጥብ 8 ሰዎችን ህይወት የሚቀጥፍ በመሆን ቀጣዩን ደረጃ ሲይዝ በስራ ቦታ ያለ ብክለት ደግሞ የ800 መቶ ሺህ ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት እንደሆነ ተነግሯል፡፡

92 በመቶ በብክለት ሳቢያ የሚከሰት ሞት በደሃ ሀገሮች የሚከሰት እንደሆነም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ከእነዚህም ውስጥ እንደ ህንድ ባሉ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በሚታይባቸው አገሮች ላይ ችግሩ በይበልጥ ጎልቶ እንደሚወጣ ተገልጿል፡፡

በአለም እ.ኤ.ኤ በ2015 ብክለት የ9 ሚሊዮን ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ ይነገራል፡፡

ምንጭ፦ቢቢሲ