ደኢህዴን ለክልሉ ህዝቦች ህገ መንግስታዊ ዋስትና ማስገኘቱ ተገለጸ

ጥቅምት 10፤2010

በሀዋሳ ከተማ በመከበር ላይ የሚገኘው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) 25ኛ ዓመት የብር ኢዮበልዩ በአል አካል የሆነው አውደ ጥናትም ዛሬ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች በተገኙበት ተከፍቷል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ "የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ደኢህዴን ያለፉት 25 ዓመታት የትግል ጉዞ እና የቀጣይ ሩብ ምእተ ዓመት ስትራቴጂያዊ አቅጣጫ" የሚል ሰነድ በአቶ ተስፋዬ በጅጌ የደኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ ፅፈት ቤት ሀላፊ ለውይይት ቀርቧል፡፡

በአውደ ጥናቱ ደኢህዴን የተመሰረተበት አላማ በህዝቦች ለዘመናት የነበረውን ጭቆና ለመቀልበስ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከደርግ መንግስት ውድቀት ማግስት ደኢህዴን ኢህአዴግ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ህገመንግስታዊ ዋስትና አስግኝተዋል ተብሏል፡፡

በተለይም ፆታዊ እኩልነትን ከማረጋገጥ አንፃር ድርጅቱ ባለፉት 25 ዓመታት በርካታ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ ለአብነትም በ1987 ዓ.ም ሴቶች በክልሉ በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ 19.4 በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ይህን አሀዝ ወደ 29.7 በመቶ ማሳደግ ተችሏል፡፡

ደኢህዴን በቀጣይ 25 ዓመታት ራእይ ስትራቴጂያዊ የትግል አቅጣጫዎች ጠንካራ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት መገንባት፣ የጥልቅ ተሀድሶውን በማስቀጠል የፖለቲካል ኢኮኖሚውን ልማታዊ ማድረግ፣ የህዝብ አቅምን መገንባትና መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግን ያካተተ እንደሆነም በአውደ ጥናቱ ላይ ቀርቧል፡፡

በአሉ በስፖርታዊ ውድድሮች፣ ድርጅታዊ ኮንፍረንሶችና አውደ ጥናቶች ከነሀሴ 2009 ዓ.ም ጀምሮ ሲከበር ቆይቷል፡፡

በናትናኤል ፀጋዬ