በምርት ሽያጮች ላይ ያለአግባብ ዋጋ በመጨመር የተለዩ ነጋዴዎች ሊከሰሱ ነው

ጥቅምት 9፣2010

ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖራቸው በምርት ሽያጮች ላይ የዋጋ ጭማሪ አድርገው በተለዩ  ነጋዴዎችን ላይ ክስ ለመመስረት መዘጋጀቱን የንግድ ውድድር እና የሸማቾት ጥበቃ ባለስልጣናት አስታወቀ፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ የሚመረቱ እና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጭማሪ መታየቱን ባለስልጣኑ ባደረገው ዳሰሳና የህብረተሰብ ጥቆማ ማረጋገጡን አመልክቷል፡፡

በተለይ የኤሌክትሮኒክስ እና የግንባታ ዕቃዎች ሰፊ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡

በመሆኑም ባለስልጣኑ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ከህብረተሰቡ በተገኙ ጥቆማዎች እና በዳሰሳ በተለዩ ነጋዴዎች ላይ ክስ ለመመስርት ልየታ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ ለኢቢሲ እንደተናገሩት ከምንዛሬ ተመን ማሸሻያ ጋር በተየያዘ  በአንዳንድ ዕቃዎች ላይ የሚኖር ጭማሪ ከሁለት ወር እና ሶስት ወር በሃላ መከሰት ሲገባው ፣በአሁኑ ሰዓት የሚደረግ ጭማሪ በምንም ሚዛን ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡

በተለይ በግብርና ምርቶች ዘርፍ በቂ ምርት ባለበት ሁኔታ የዋጋ ጭማሪ ሊኖራቸው እንደማይገባ ባለስልጣኑ አሳስቧል

በቀጣይም በገበያው ላይ አላስፈላጊ ሀብት መሰብሰብ የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ወደ ህግ ለማቅረብ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን  አቶ እንዳልካቸው ገልጸዋል፡፡

ህ/ሰቡ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን በ8478 በመጠቆም ማጋለጥ እንደሚቻል ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡

በአዝመራው ሞሴ