የተመድ ዋና ፀሀፊ በማዕከላዊ አፍሪካ ተጨማሪ 9 መቶ ሰላም አስከባሪዎች እንዲሰማሩ ጠየቁ

ጥቅምት 9፣2010

የተመድ ዋና ፀሀፊ በማዕከላዊ አፍሪካ ተጨማሪ 9 መቶ ሰላም አስከባሪዎች እንዲሰማሩ ጠየቁ፡፡

አሜሪካ የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይል  ወጭ እንዲቀንስ እየጠየቀች ባለበት ወቅት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በማዕከላዊ አፍሪካ ሰላማዊ ዜጎችን ለመጠበቅ ተጨማሪ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡

ጉቴሬዝ ጥያቄውን የፀጥታው ምክር ቤት ተመልክቶ ከእርስ በርስ ግጭት ያልወጣችውን የመካከለኛው አፍሪካ ንፁሃን ዜጎችን ህይወት ለመጠበቅ ይሁንታውን ይሰጣል ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡

ዋና ፀሃፊው አገሪቱንም በቀጣዩ ሳምንት ለመጎብኘት እቅድ መያዛቸውን ሮይተርስን ጠቅሶ ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

25 በመቶውን የተመድን የሰላም አስከባሪ ኃይል ወጭ በ28 በመቶ  ለመቀነስ አሜሪካ ማሰቧ "ፍትሃዊ ሀሳብ" አለመሆኑንም ጉቴሬዝ አመልክተዋል፡፡

የጉቴሬዝ ጥያቄ ተቀባይነት ለማግኘት በፀጥታው ምክር ቤት ፊት ቀርቦ የአሜሪካን ይሁንታ ጭምር ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡

በአሁኑ ግዜ እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ 12ሺ ሰላም አስከባሪዎች በማዕከላዊ አፍሪካ ተሰማርትው የሚገኙ ሲሆን፣ በአገሪቱ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ችግሩ እየገዘፈ በመምጣቱ ተጨማሪ ኃይል የተጠየቀው፡፡

ተመድ በአለም ላይ ላሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል በየአመት 7.3 ቢሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስወጣው ዘገባው ያትታል፡፡