በጅማ ዞን በህገ-ወጥ መንገድ በባለሃብቶች ተይዞ የነበረ ከ4ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ተመለሰ

ጥቅምት 03፣2010

በጅማ ዞን በህገ-ወጥ መንገድ በባለሃብቶች ተይዞ የነበረ አራት ሺህ ሁለት መቶ ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት ለመንግስት መመለሱን የዞኑ አስተዳደር ገለፀ፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብድልሀኪም ሙሉ በዞኑ በተለይም ሊሙ ኮሳ በተባለ ወረዳ አርባ ሶስት ባለሀብቶች ይዞታቸውን ለማስፋፋት ሲሉ የደን ጭፍጨፋ ማካሄዳቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

በህገ-ወጥ መንገድ በባለብቶቹ የተያዘውን አራት ሺህ ሁለት መቶ ሄክታር መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲመለስ መደረጉን ዋና አስተዳዳሪው አቶ አብዱልሀኪም አብራርተዋል፡፡

በጅማ ዞን ሶስት መቶ ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደን መኖሩን የዞኑ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡