ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር ትፈልጋለች- ጠ/ሚ/ር ሃይለማሪያም ደሳለኝ

ጥቅምት 02፤2010

ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ የግብጽ አረብ ሪፐፕሊክ አምባሳደር ከሆኑት አቡበከር ሄፍኒ ጋር ነው በጽህፈት ቤታቸው የተወያዩት᎓᎓

በውይይቱ ወቅት  ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከግብጽ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር ትፈልጋለች᎓᎓

የሁለቱ ሃገራት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት መልካም ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል᎓᎓

አምባሳደር  አቡበከር ሄፍኒ በበኩላቸው የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ በቅርቡ የተስማሙበትንና የተፈራረሙበትን ጉዳዮች ማጠናከርና እውቅና መስጠት ይገባናል ብለዋል᎓᎓

ከተካሄደው ውይይት ለመረዳት እንደቻለው ሁለቱ ሃገራት በንግድ በኢንቨስትመንት በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በጤና በፋርማሲ ኢንዱስትሪ የሃኪሞች የልኡካን ቡድን በመላክ የኢንዱስትሪል ዞኖችን በማቋቋም እና በግብርና ኢንቨስትመንት ለመተባበር ተስማምተዋል᎓᎓

ከዚህ በተጨማሪም በግብጽና በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ከዚህ ቀደም የተፈረሙትን ስምምነቶች ወደ ተግባር ለመለወጥ ጠንክረው እንደሚሰሩ ነው የተገለጸው᎓᎓

በተያያዘ ዜና በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ታዬ አጽከስላሴ ከግብጽ መገናኛ ብዙሃን አል ማስሪ አል ዩም ጋር ባደረጉት ንግግር ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ቴክኒካል ጉዳዮችን መፍታት በጋራ ስምምነት እንዲፈታ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም የግብጽ ቴክኒካል ኮሚቴ አባላት የህዳሴ ግድቡን ይጎበኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር