በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ልጃገረዶች ጥበቃ እዲደረግላቸው ተጠየቀ

ጥቅምት 1፤2010

ከሳሃራ በታች ባሉ አፍሪካ ሀገሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ልጃገረዶች ጥበቃ እዲደረግላቸው የተባበሩት መንግስታት የህፃናት መርጃ ድርጅት /ዩኒሴፍ/ ጥሪ አቀረበ፡፡

በድርጅቱ የምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና ደይሬክተር ለይላ ፓካላ አለም  አቀፉ የልጃገረዶች ቀን በማስመልከት እንደገለጹት በቀጠናው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጃገረዶች በእርስ በርስ ግጭቶችና በአፍሪካ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት መሰረታዊ የሚባሉ መብቶቻቸው ሳይከበር  ቀርቷል፡፡

በግጭት ወቅት ከወንዶች ይልቅ ልጃገረዶች በ2.5 እጥፍ ከትምህርት ቤት ውጭ ይሆናሉ፤ ለያለ እድሜ ጋብቻ ይጋለጣሉ ተብሏል።

ለይላ ፓካላ እንዳሉት ልጃገረዶችን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን ብለዋል።

ዩኒሴፍ እንደገለፀው በጥቃት ሚክንያት በየአስር ደቂቃው አንድ ልጃገረድ ትሞታለች፤ በእርስ በርስ ግጭቶች ወቅትና ከግጭቶች በኋላ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጃገረዶች ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ፡፡ 

ችግሩን ለመፍታት የልጃ ገረዶችን አቀም ማጎልበት፣ አስቸኳይ ምላሽ  እና በልማት ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገ ኢንቨስትመንትና ትብብር ያስፈልጋል ተብሏል።

ባለፈው አመት በአለም ላይ 535 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት ግጭት፣ የተፈጥሮ እና ሌሎች አደጋዎች በተጎዱ አገራት ይኖሩ ነበር።  ከዚሁ ሶስት አራተኛ የሚሆንኑት ከሰሀራ በታች የሚኖሩ መሆናቸው ዩኔሴፍ አመልክቷል ሲል የዘገበው ሽንዋ ነው።