ማሕበሩ አደጋዎችን መከላከል የሚችል ማህበረሰብ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ከፕ/ት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ

መስከረም 30፤2010

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ችግርን ቀድሞ የሚቋቋም ማሕበረሰብን በመፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ፡፡

ዶክተር ሙላቱ በዓለም የቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማሕበራት ፌዴሬሽን ምክትል ዋና ፀሐፊ ዶክተር ጀሚላ ማሆድ የሚመራ የለጋሾች መማክርት አባላት ልዑካንን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

በውይይታቸው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ከዓለም አቀፍ ተቋም ጋር በመሆን ድርቅን ተከትሎ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለማቅረብ በሚያካሂዳቸው ተግባራት ዙሪያ መክረዋል፡፡

በተለይ ውኃ አጠር በሆኑ አካባቢዎች የውኃ አማራጮችን በማስፋት ድርቅ መቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት ላይ መወያየታቸውን የልዑካን ቡድኑ መሪ ገልፀዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታን ተከትሎ በሚቀርብ የዕለት ድጋፍ ላይ ብቻ ሳይሆን ችግርን የሚቋቋም ማሕበረሰብ መፍጠር የሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት መግለፃቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የፕሬዝዳንት ፅሕፈት ቤት የኮሚኒኬሽንና ፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ፕሬዝዳንት ዶክተር አህመድ ረጃ የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት ማሕበሩ ኢትዮጵያ ለምታከናውናቸው የሰብአዊ ዕርዳታና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአየለ ጌታቸው