በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል አመራሩ ጠንክሮ እንዲሰራ ተጠየቀ

መስከረም 27፣2010      

በጋምቤላ ክልል የኤች አይ ቪ ኤድስን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት አስታወቁ፡፡

በክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ውስንነት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

በክልሉ የኤች.አይ.ቪ ስርጭትን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማጠናከር የሚያስችል የአመራርና የባለድርሻ አካላት የጋራ የምክክር መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ጋትሉዋክ ቱት በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ እየተስፋፋ የመጣውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው።

ጥረቱ ውጤታማ እንዲሆን በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አካላት ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን በሽታውን ለመከላከል ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ጋትሉዋክ እንዳሉት፣ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የኤች.አይ.ቪን ስርጭት ለመከላከል በተከናወኑ ሥራዎች የስርጭት መጠኑ ቀደም ሲል ከነበረበት 6 ነጥብ 5 በመቶው ወደ 4 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተችሏል፡፡

"አሁንም ቢሆን የበሽታው ስርጭት መጠን በከፍተኛ ደረጃ የሚገኝ በመሆኑ በሽታውን የመከላከል ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ብለዋል፡፡

ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የፌደራል ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብረሃም ገብረመድህን በበኩላቸው የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተጠያቂነትን በተላበሰ መልኩ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡ 

አመራሩ በቁርጠኝነት ከሰራ በክልሉ ያለውን የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ጽህፈት ቤቱ ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በክልሉ የኤች.አይ.ቪ /ኤድስን ስርጭት ለመግታት እየተደረጋ ያለውን ጥረት ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በእኔነት ስሜት ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል፡፡

በተለይ የሃይማኖት ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ሌሎችም አካላት በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

የበሽታውን ስርጭርት ለመግታት ሁሉን አቀፍ የማህብረሰብ ውይይት በሰፊው መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አመላክተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡