የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎችና የሰው ኃይል እጥረት በስራው ላይ ጫና እንደፈጠረበት አስታወቀ

መስከረም 21፣2010

የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል የህክምና መሳሪያዎችና የሰው ኃይል እጥረት በአስከሬን ምርመራ ስራው ላይ ጫና እንደፈጠረበት አስታወቀ፡፡

የዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ለበርካታ አስርት ዓመታት የአስከሬን ምርመራ አገልግሎት በአገር አቀፍ ደረጃ በብቸኝነት በማገልገል በመላ አገሪቱ ያሉ ተቋማት፣ግለሰቦችና ሌሎች አካላት አገልግሎቱን ለማግኘት ረጅም ርቀት በመጓዝ ለገንዘብና ለጊዜ ብክነት እየተጋለጡ ናቸው።

እንዲያም ሆኖ ሆስፒታሉ ምርመራውን ሳይንሱ በሚያዘው መሰረት ማከናወን የሚያስችሉ የህክምና መሳሪያዎችና በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይል አለመያዙ በስራው ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ ማሳደሩን ገልጿል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤  የአስክሬን ምርመራው በዘመናዊ አሰራርና በተደረጀ የሰው ኃይል ያለመካሄዱ ስራውን የተቀላጠፈ እንዳይሆን አድርጎታል ።

በቀን በአማካኝ ከ10-15 ወይም በወር እስከ 300 የአስክሬን ምርመራ አገልግሎት ፈላጊዎች ወደ ሆስፒታሉ እንደሚመጡ የገለጹት አቶ አለምአየሁ ፍላጎቱና የሆስፒታሉን አቅም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምንም አይነት ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም ብለዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበኩሉ የሰው ኃይልና ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን እጥረት ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አሚር አማን እንዳሉት በአገሪቱ  ከዚህ ቀደም ከወንጀል ነክ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን  ምርመራዎች  ለማደረግ የሚስያችል የሐኪሞች የስፒሻሊስት ስልጠና አለመኖር ለሰው ሃይሉ ዕጥረት ዋነኛ ችግር ነው።

ሚኒስቴሩ ችግሩን ለመፍታት የአስከሬን ምርመራ አገልግሎቱን ከአዲስ አበባ ውጪ እንዲሰጥ ከመስራቱም በላይ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሃይልና አገልግሎቱን መስጠት የሚያስችሉ የህክምና መሳሪያዎችን ግዢ በማከናወን ላይ መሆኑንም ዶክተር አሚር ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት ደግሞ ተጨማሪ ስምንት ሐኪሞች ወደ ስፔሻላይዜሽን ስልጠና እንደሚገቡም አክለዋል።

ከሚኒሊክ ሆስፒታል በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ከህግ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አገልግሎቶች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።