ኢትዮጵያ በኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ከፍተኛ ደረጃ መያዟ ተገለጸ

መስከረም 19፣2010

ኢትዮጵያ በኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ከሠሀራ በታች ካሉ ሀገራት ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል ከፍተኛውን ደረጃ መያዟን የጳውሎስ ኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል አስታወቀ፡፡

የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሞሚና ሃመድ እንደተናገሩት፤ ማዕከሉ ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ከሰሐራ በታች ካሉ አገሮች ውጤታማ የሆነ የኩላሊት ንቅለ ተከላዎችን ለማከናወን ችሏል። 

ማዕከሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት 50 የኩላሊት ንቅለ ተከላዎችን ሲያከናውን ከእነዚህ ውስጥ የአርባ ዘጠኙ ኩላሊት በሙሉ ጤንነት መስራት እንደቻለም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ለማግኘት የተመዘገቡና ለጋሽ ያገኙ 25 ህሙማን ያሉ መሆኑን ገልጸው፤ በበጀት ዓመቱ ለ50 ሕሙማን ህክምናውን ለመስጠት መታቀዱን አመልክተዋ።

በአሜሪካ ሚችጋን ዩንቨርሲቲ የቀዶ ህክምና ፕሮፌሰር  ሚስተር ጄፍ ፓንች የኩላሊት ንቅለ ተከላው ውጤታማነቱ ከሚችጋን፣ ቦስተን ፣ ፓሪስ ፣ ሆንግ ኮንግ ጋር ሲነጻጻር "ተመሳሳይ ነው" ነው ብለዋል።

ህክምናው ውጤታማ እንዲሆን የጤና ጥበቃ ሚንሰቴር፣ በጤናው ዘርፍ ያሉ አካላት፣ የማዕከሉ የህክምና ባለሙያዎች ያደረጉት የጋራ ጥረምት አድንቀዋል።

በኮሌጁ የህክምና አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኤ በበኩላቸው በኮሌጁ የንቅለ ተከላ መርሃ ግብር መጀመሩ የህክምና አገልግሎቶች እንዲሻሻልና ቀደም ሲል ያልነበሩ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ አስችሏል ብለዋል።

በኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናው አራት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሰልጥነው የህክምናውን 90 በመቶ እያከናወኑ ይገኛሉ።

በሁለተኛ ዙር የስልጠናው መርሃ ግብር አስር ባለሙያዎች በስልጠና ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቅርብ ጊዜ ውስጥ ህክምናውን ሙሉ ለሙሉ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለማከናወን ታቅዷልም ብለዋል።

እንደ ዶክተር ብርሃኔ ገለጻ፤ በውጭ ሀገር ህክምናውን ለማከናወን ከአራት መቶ እስከ አምስት መቶ ሺ ብር የሚፈጅ ሲሆን፤ ማዕከሉ ከድህረ ንቅለ ተከላ ጀምሮ የንቅለ ተከላውን ህክምናና የሁለት ወር መድሃኒት በነጻ እየሰጠ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ ህግ የሚፈቅደውና እየተሰራበት ባለው መመሪያ መሰረት ኩላሊት መለገስ የሚቻለው የደም ወይም የጋብቻ ዝምድና ባላቸው ሰዎች መካከል ብቻ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ከስድስት ወር በፊት ለእህቷ አንዱን ኩላሊቷን የለገሰችው ወጣት ሜሮን ደምሴ በቦታው ተገኝታ እደገለጸችው፤ ኩላሊትን ከለገሰች በኋላ ሕክምናውን በሚገባ እየተሰጠ በመሆኑ "በቀሪው ኩላሊት በጤንነት እየኖርኩ ነው" ብላለች።

ሌላዋ ለጋሽ ወይዘሪት አለምሸት ግርማ እንዳለችው  ''መጀመሪያ ለልግስናው ስትዘጋጂ ውሳኔ ያስፈልጋል፤ ከዚያም የሰውን ሕይወት የማዳን በጎ ተግባር በመሆኑ የሕሊና እረፍት ይሰጣል" ብላለች።