የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

መስከረም 15፣2010

የአለም አየር ንብረት ለውጥ በቡና ምርታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ በመምጣቱ የአንስተኛ ማሳ አርሶ አደሮች ለጉዳት እየተጋለጡ እንደሆነ አለም አቀፉ የቡና ድርጅት አስታወቀ፡፡

በየጊዜው የአለም ሙቀት መጨመርና የእርጥበት መጥን መቀያየር ለዚህ ችግር መፈጠር ዋንኛ ምክንያት እንደሆኑ ተነግሯል፡፡

የአየር ንብረት ለውጡ በዚህ ከቀጠለ በምዕተ ዓመቱ መጨረሻ የምርቱ መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ የቡና ሰብል ማብቀያ ማሳዎች በ60 በመቶ እንደሚቀንሱ ተገልጿል፡፡

በአለም የቡና ቁጥር አንድ አምራች እንደሆነች በሚነገርላት ብራዚል ደግሞ የሀገሯ የሙቀት መጠን በ1 ነጥብ 2 ድግሪ ሴንቲግሬድ መጨመሩን ተከትሎ 2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነውን የምርቱን ማብቀያ ማሳ በ7 በመቶ ለመቀነስ ማሰቧን ተሰምቷል፡፡

በምድር ወገብ ደጋማ አካባቢ የሚበቅለውና 60 በመቶ የአለም የቡና ምርትን የሚሸፍነው ‹‹አረቢካ ኮፊ›› የሚባል የቡና ዝርያ ለመብቀል ከ18 እስከ 21 ድግሪ ሴንትግሬድ የሙቀት መጠን ቢስማማውም አሁን ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ለአደጋ እንዳያጋልጠው ያስፈራል ተብሏል፡፡ 

በአለም 21 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች በቡና ግብርና ላይ የተሰማሩ ቢሆንም 85 በመቶ የሚሆነው ምርት የሚመረተው አነስተኛ ማሳ ባላቸው አርሶ አደሮች እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

ምንጭ፦ ፋይናንሺያል ታይመስ ድረ-ገጽ