በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ያለው ውጥረት በውይይት እንዲፈታ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጠየቁ

መስከረም 12፣2010

የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በኮሪያ ባህረ ሰላጤ ያለው ውጥረት በውይይትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ጠየቁ፡፡

ዶክተር ወርቅነህ የአውዳሚ መሳሪያዎች ቁጥጥር ላይ የተነጋገረውን የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባን በሊቀመንበርነት በመሩበት ወቅት እንዳሉት፣ አውዳሚ መሳሪያዎች ለአለም ሰላምና መረጋጋት ስጋት ናቸው፡፡

በተለይም እንደዚህ አይነት የባሌስቲክ ሚሳይልና ኒውክሊየር የመሰሉ አውዳሚና ገዳይ መሳሪያዎች አሸባሪዎችና ጽንፈኞች እጅ ከወደቀ በአለም ላይ የከፋ ጥፋት ይከሰታል ብለዋል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሬክ ቴሌርሰን በበኩላቸው አለም ከኒውክሊየር ስጋት የሚመነጭ አደጋ አንዣብቦባታል ካሉ በኃላ አለም አቀፍ ማኅበረሰብ በሰሜን ኮሪያ ላይ ጫና እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በስብሰባው የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትርን ጨምሮ የበርካታ አገሮች አቻዎቻቸው ንግግር አድርገዋል፡፡

ቀደም ሲል በአይ ኤስ አይ ኤስ ጉዳይ ላይ በተጠራው ስብሰባ በመከሩበት ወቅት ዶ/ር ወርቅነህ፣ አይ ኤስ ኤስ የተባለው የአሸባሪ ቡድን ሊቢያ ላይ በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸመው ኢሰብአዊ ተግባር ተጠያቂ እንዲሆን አፅንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል።

ሚንስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ምክር ቤቱ ውሳኔውን በሙሉ ድምጽ ማሳለፉ፣ አሸባሪነትንና ጽንፈኝነትን ለመዋጋት አስተዋጽኦው ከፍ ያለ እንደሆነም ገልጸዋል።

ምንጭ:-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር