የአፍሪካን ግብርናን ለማሳደግ ኢትዮጵያ ልምዷን ታካፍላለች፦ጠ/ሚ ኃይለማርያም

መስከረም 12፣2010

የአፍሪካን ግብርና ለማሳደግ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ተሞክሮ ለማካፈል ዝግጁ መሆኑዋን ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡

በ72ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እየተሳተፉ ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከቢልና ማሊንዳ ፋውንዴሽን መስራችና ሊቀመንበር ቢል ጌትስ ጋር በአጠቃላይ የአፍሪካ የግብርና ልማት መርሀ ግብር ማሻሻያ ስራዎች ዙሪያ መክረዋል፡፡

የአፍሪካ ግብርናን ለመለወጥ እ.አ.ኤ በ2014 ይፋ በሆነው የአፍሪካ ህብረት የማላቡ ስምምነት የውይይቱ የትኩረት መስክ ነበር ተብሏል፡፡

ግብረ ሰናይ ድርጅቱ የአፍሪካን የግብርና ምርታማነት ለመጨመረ በሚያደርገው ጥረት በዘርፉ የአፍሪካ ሀገራት አፈፃፀም ለመገምገም የሚያስችል መለኪያዎችን እንደሚዘረጋ ቢል ጌትስ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የግብረ ሰናይ ድርጅቱን እቅድ ለመደገፍ ያላቸውን ዝግጁነት በመግለጽ በዘርፉ የኢትዮጵያን ልምድ ለአፍሪካዊያን ለማካፈል ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ለወጣቶችና ሴቶች ትኩረት በመስጠት ህዝብ ተኮር በሆነ መልኩ የአህጉሪቱን የ2063 አጀንዳን ዳር ለማድረስ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ግብረ-ሰናይ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በሚያደርገው የልማት ተሳትፎ በቤተሰብ ጤናና በግብርና ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ነው የሚባለው፡፡

የቢልና ማሊንዳ ግብረ ሰናይ ድርጅት በ45 የአፍሪካ ሀገሮች በተለያዩ መርሀ ግብሮች ድጋፍ ያደርጋል፡፡

ምንጭ፦ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር