በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ለማሳደግ የሚረዳ ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

መስከረም 12፣2010

በዓለም የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም UNESCO ድጋፍ በምሥራቅ አፍሪካ ያለውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ለማሳደግ "የተሻለ ትምህርት ለአፍሪካ እድገት" በሚል ለአምስት አመታት የሚቆይ ፕሮጀክት ሊተገበር ነው፡፡

ፕሮጀክቱን ለመተግበር የሚያስችል የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት ላይም ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ በኢትዮጵያ ያለውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ጠቀሜታ፣የትምህርት አሰጣጥ ጥራትና ሕብረተሰቡ ለቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ያለውን አመለካከት የሚዳስስ ሪፖርት ቀርቧል፡፡

ከውይይቱ በሚነሱ ሀሳቦች ዳብሮ ፕሮጀክቱ በዩኔስኮና በደቡብ ኮሪያ ድጋፍ ከ5 ወራት በኋላ በኢትዮጵያ የሚተገበር ይሆናል፡፡

ፕሮጀክቱ በተለይም በማምረቻው ዘርፍ እና የእርሻ ማቀነባበሪያ መስኮች ላይ ትኩረት ያደርጋል፡፡ ለፕሮጀክቱም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ተመድቧል፡፡

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በኬንያ፣በኡጋንዳ፣ማዳጋስካርና በታንዛኒያ እንደሚተገበር ታውቋል፡፡

ዘገባው የሪፖርተራችን ኢየሩሣሌም በፀሀ ነው፡፡