የጸጥታው ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር ጥረት አደነቁ

መስከረም 11፣2010


በ72ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ የተገኙ የጽጥታው ምክር ቤት አባላት የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር እንቅስቃሴ አድንቀዋል፡፡


የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ ኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር የውሳኔ ማሻሻያ ሃሳብ ማቅረቧ፣ ድርድሩን መምራቷና ያቀረበችው የውሳኔ ሃሳቡ በሙሉ ድምጽ መጽደቁ መድረኩን ለየት ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኬ በበኩላቸው ስብሰባው በኢትዮጵያ ፕሬዝዳንትነት በመካሄዱ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ ለአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ላበረከተችው ጉልህ አስተዋጽኦዋ በአፍሪካ ህዝቦች ስም አመስግነዋል፡፡


የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬሳ ሜይ ኢትዮጵያ የአለም ሰላም ሻምፕዮን ናት ያሉ ሲሆን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ፔትሮ ፖሮሸንኮ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር መስክ በወርቅ የተጻፈ ታሪክ አላት ብለዋል፡፡


የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስም እንዲሁ ኢትዮጵያ ይህንን መድረክ ማዘጋጀቷ ለአለም ሰላም ያላትን ተዋናይነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግብጹ ፕሬዝዳነት አልሲሲም እንዲሁ ኢትዮጵያ ይህንን መድረክ በማዘጋጀቷ ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል፡፡