የቡና ምርት ግብይት አበረታች ለውጥ አሳይቷል፦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ

መስከረም 11፣2010

ባለፉት ሁለት ወራት በቡና ምርት ግብይት አበረታች ለውጥ መመዝገቡን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አስታወቀ፡፡

ወደ ምርት ገበያው የሚቀርበውን የቡና ምርት መጠን ለመጨመርም ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የቡና ምርት ግብይት ማሻሻያ ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ነፃነት ተስፋዬ በተለይ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡                         

ቀደም ሲል የነበረው የቡና ግብይት ስርዓት የምርቱ አቅራቢዎች ቡናቸውን መጋዘን ካቀረቡ በሃላ ግብይት የሚፈፀም በመሆኑ የምርቱን ግብይት ያዳከመ ነበር ብለዋል፡፡

ችግሩ ለመቅረፍም ድርጅቱ ከቡና አቅራቢዎችና ላኪዎች በቀረበለት ሀሳብ መሰረት የቡና ማሻሻያ ግብይት ስርዓት በመዘርጋት የቡና ምርቱ መጋዘን ከመግባቱ በፊት የተመረተበት ቦታና የአቅራቢው ስም ተገልጾ መኪና ላይ ግብይቱ እንዲፈፀም መደረጉን ገልፀዋል፡፡

ግብይቱ በመኪና ላይ እንዲፈፀም መደረጉ አምራቾችና አቅራቢዎች ለመጋዘን ክፍያ የሚያወጡትን አላስፈላጊ ወጪ እንዲቀንስ ማድረጉ ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑን አቶ ነጻነት ተናግረዋል፡፡

የቡና ግብይት ማሻሻያው ከተጀመረ ከሁለት ወር ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የቀረበው የምርት መጠን መጨመሩንም አቶ ነፃነት ጠቁመዋል፡፡

ለአብነትም ባለፈው ሐምሌ ወር በድርጅቱ ለግብይት የቀረበው ቡና 13 ሺህ 927 ሜትሪክ ቶን ሲሆን ይህ አህዝ በወርሀ ነሐሴ ወደ 21 ሺህ 159 ሜትሪክ ቶን አሻቅቧል ብለዋል፡፡

የአዲሱ አሰራር ለውጥን ተከትሎ በምርት ገበያው አባል ያልሆኑ አርሶ አደሮች፣ ህብረት ስራ ማህበራትና የንግድ ድርጅቶች በቡና ግብይት ስርዓቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ መደረጉን አመልክተዋል ስራ አስኪያጁ፡፡

ሪፖርተር፦ ሰለሞን አብርሃ