የአለም መሪዎች በትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ

መስከረም 11፣2010

በ72ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኒውዮርክ የሚገኙ የአገራት መሪዎች በትምህርት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸው ገልጸዋል።

መሪዎቹ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ህጻናት የትምህርት እንቅፋት እየሆነ ያለው የፋይናንስ ችግር ለመፍታት ያለመ ውይይት አድርገዋል።

በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2030 በትምህርት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ፋይናንስ እናድረግ በሚል መሪ ቃል በተካሄደው የትምህርት ውይይት ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቴኒዮ ጉተሬዝ ለትምህርት የሚደረግ ኢንቨስትመንት ወደፊት የተሻለ አለም ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።

ከ260 ሚሊዮን በላይ ህጻናት፣ ወጣቶችና ጎልማሶች ከትምህርት ውጭ መሆናቸውን ተገልጿል።

በአንዳንድ ድሀ አገራት የስርአተ ጾታ እኩልነት ላይ መሻሻል ቢታይም አሁንም ሴቶች ከወንዶች እኩል የትምህርት እድል እንደማያገኙ በውይይቱ ተመልክቷል።

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ሴቶች ድህነት፣ ጦርነትና ያለ እድሜ ጋብቻ  ከትምህርት እያስቀሯቸው መሆኑ ተገልጿል።

በመንግስታት፣ የግል ዘርፍ፣ በሲቪል ማሕበራት እና በመንግስታቱ ድርጅት ትብብር በተካሄደው ውይይት በመዋእለ ህጻናት፣ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ጥራት ያለው ትምህርት ለማምጣት የፖለቲካ ቁርጠኝነትና በትምህርት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተሰምሮበታል።

ምንጭ፤ ተመድ