የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የተመድ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ ማሻሻያ ሀሳብ አፀደቀ

መስከረም  10፣2010

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የተመድ የሰላም አስከባሪ ተልእኮ ማሻሻያ ሀሳብን አፀደቀ።

ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት እያደረገ ባለው ልዩ ስብሰባው ላይ ነው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ አፋጣኝ ማሻሻያ እንዲደረግ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሀሳብ በሙሉ ድምፅ ያፀደቀው።

በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ኢትዮጵያ እንደመሆኗ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስብሰባውን በፕሬዝዳንትነት መርተዋል።

በስብሰባው ላይ የተለያዩ አገራት ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች እና አምባሳደሮች ተገኝተዋል።

የማሻሻያ ሀሳቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም ማስከበር ስራ ውጤታማ እንዲሆን እንዲሁም ለሰላም ማስከበር ለሰላም አስከባሪው ጦር አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ሊሟሉለት እንደሚገባ የሚጠይቅ ነው።

የማሻሻያ ሀሳቡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን መካከልም አጋርነት መኖር እንዳለበት የሚያመላክት ሲሆን፥ በተለይም በፀጥታው ምክር ቤት ስር በአፍሪካ ህብረት የሚመራው የሰላም አስካባሪ ሀይል በምን መልኩ የገንዘብ ድጋፍ ሊደረግለት እንደሚገባም ይደነግጋል።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የውሳኔ ሀሳቡ መፅደቅ በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ በላይ የሰላም አስከባሪ ሀይል በተለያዩ አከባቢዎች ላሰማራችው ኢትዮጵያ ልዩ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ ማሻሻያውን በተገቢው መልኩ እንዲተገብርም  አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በተመድ የሰላም ማስከበር ጥላ ስር በዳርፉር፣ አብዬ እና ደቡብ ሱዳን የሰላም አስከባሪዎችን አሰማርታለች።

ሪፖርተር :-እናትአለም  መለሰ (ከኒውዮርክ)