ወቅቱ የወባ ስርጭት የሚኖርበት በመሆኑ ቅድመ ዝግድት ተደርጓል-የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር

መስከረም 08፣2010

የክረምቱን ዝናብ ተክትሎ የሚኖረውን የወባ ስርጭት ለመከላከል ሰፊ ዝግጅት ማድረጉን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በበሽታዎች መካላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የወባ ባለሞያ አቶ ደረጀ ጌድኦ ለኢቢሲ እንደተናገሩት ወቅቱ ከፍተኛ የወባ ስርጭት የሚኖርበት በመሆኑን የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ተደርገዋል።

ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሁለት አይነት ኬሚካሎች ተገዝተው ወደ ክልሎች ተሰራጭተዋል፤ የቤት ውስጥ ርጭትም እየተካሄደ ነው ብለዋል ባለሞያው።

ባለፉት ሁለት አመታት ከ32 ሚሊዮን በላይ አጎበሮች ተሰራጭተዋል ያሉት አቶ ደረጀ ህብረተሰቡ የአጎበር አጠቃቀሙን እንዲያሻሽልና እጁ ላይ ያለው አጎበርም በአግባቡ እንዲጠቀም ትምህርት እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡

አጎበሮቹ ሕብረተሰቡ ለሶስት አመታት ብቻ ሊጠቀምበት እንደሚገባ ጠቁሟል።

ሕብረተሰቡም የክረምቱን ዝናብ ተከትሎ የሚመጣው ውሀ ማቆር ጉድጋዶች መድፈን በቤት ውስጥ የሚገኙ ሰባራ ዕቃዎችን የማስወገድ ስራ እንዲሰራ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ደረጀ ገልጸዋል።

ባለፉት ስምንት አመታት በአገሪቱ የነበሩ የወባ ስርጭት ወረዳዎች ከ68 ወደ 60 ከመቶ መቀነሱን ገልጸው ከአየርን ብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ከፍተኛ ቦታዎች የወባ ስርጭታቸው እንዳይጨምር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የአገሪቱ ዝቅተኛ ቦታዎች እንዲሁም ከፍተኛ የልማት ስራ የሚካሄድባቸው አከባቢዎችም ከፍተኛ የወባ ስርጭት የሚታይባቸው መሆናቸው ተመልክቷል።

ከፍተኛ የልማት ስራዎች ወደ ሚከናወኑባቸው አከባቢዎች በየአመቱ አስር ሚሊዮን ብር በመመደብ ጊዚያዊ የሰራተኞችን ህክምና የሚሰጡ ጊዚያዊ ሰራተኞችን በመቅጠር እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ከአገሪቱ 75 ከመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ክፍል ለወባ ስርጭት አመቺ መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በግደይ ገብረ