በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች መንግሥት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል- ጠ/ሚንስትር ኃይለማርያም

መስከረም 06፣2010

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረው ግጭት ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች መንግሥት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገለፁ፡፡

 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለቱ ክልሎች ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየተወያዩ ነው፡፡

ለዘመናት የዘለቀውን የኦሮሚያና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሕዝቦችን በአብሮነትና በፍቅር የመኖር እሴት ለማስቀጠል የሀገር ሽማግሌዎች ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም መንግሥት በክልሎቹ አንዳንድ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰሞኑን የተፈጠረውን ግጭት የማረጋጋትና ሕግን የማስከበር ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልፀዋል፡፡

በዚህ መሠረት የአካባቢዎቹን ሰላምና ፀጥታ ወደነበረበት ለመመለስ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ዋና ዋና መንገዶች በፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ክትትል ሥር እንዲሆኑ፣ የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች የሕዝቡን ሰላም የመጠበቅና የማረጋጋት ሥራ እንዲሰሩም፣አካል በማጉደልና የሰው ሕይወት በማጥፋት የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር እንዲያውሉ አቶ ኃይለማሪያም አዘዋል፡፡

ግጭቱ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መበት ጥሰትን እንደሚያጣራም አስታውቀዋል፡፡

በሁለቱ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት የሚያባብሱ የመገናኛ ብዙኃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ይህ የማይሆን ከሆነ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስገንዝበዋል፡፡

በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ የትኛውም ግለሰብና የፀጥታ ኃይልም ተጠያቂ ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ሪፖርተር፣ ጌቱ ላቀው