ኢትዮጵያና ኬንያ የአፍሪካን የኢኮኖሚ የበላይነትን ሊረከቡ እንደሚችሉ ተተነበየ

መስከረም 05፤2010

ኢትዮጵያና ኬንያ ከዬትኛውም የአህጉሪቱ ሀገራት የበለጠ ኢንቨስትመንትን መሳብ በመቻላቸው የአፍሪካን የኢኮኖሚ የበላይነትን ከናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ሊረከቡ እንደሚችሉ ኮንትሮል ሪስክ የተባለ አጥኚ ተቋም ገለጸ፡፡

 ተቋሙ ባለፈው ሃሙስ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ባወጣው ጥናት መሰረት ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2016 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከዬትኛውም የአህጉሪቱ ሀገራት በሰፋ ልዩነት ቀዳሚ መሆን ችላለች፡፡

ኢትዮጵያ ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሃገሪቱ በአማካይ የ10 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች የቻለች ሲሆን ባለፈው አመት ደግሞ የ6 ነጥብ 5 ምጣኔያዊ እድገት ማስመዝገብ ችላለች፡፡

ኬንያ በበኩሏ ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሃገሪቱ በአማካይ የ6 ከመቶ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች የቻለች ሲሆን በዚህ አመት ደግሞ የ5 ነጥብ 4 ምጣኔያዊ እድገት ማስመዝገብ ችላለች፡፡

የተቋሙ የጥናትና ምርምር ባለሙያ ፖል ገብርኤል እንደሚሉት ከሆነ በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአፍሪካ ልምድ ያላቸው ኢንቨስተሮች በየሃገራቱ ያለውን የጸጥታ እና ደህንነት ሁኔታ ተገንዝበው የወደፊት እድላቸው መተንበይ ይችላሉ፡፡

በዚህ ሁኔታ ደግሞ ኢትዮጵያና ኬንያ ገና ያልተነኩ የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በስፋት ስላላቸው ለእንደዚህ አይነቱ ኢንቨስተሮች ቀዳሚ ምርጫ መሆን ችለዋል ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ ታላላቆቹ የኢኮኖሚ ባለቤቶች ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ በተከታታይ አመታት የኢኮኖሚ እድገታቸው በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ኢንቨስተሮችን እምብዛም መሳብ እንዳልቻሉ ነው የተገለጸው፡፡

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ናይጄሪያ የነዳጅ ዋጋ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ ሰለምና መረጋጋት ስጋት ስላለባት በፈረንጆቹ 2014 የምጣኔ ሃብት እድገቷ 6 ነጥብ 3 የነበረው በ2015 ወደ 2 ነጥብ 7 አዘቅዝቋል፡፡

የዚህ አመት እድገቷ ደግሞ ጭራሽ 1 ነጥብ 1 በመቶ ሊሆን እንደሚችል ነው የተተነበየው፡፡

ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ ዋንኛ የኢኮኖሚ መሰረቷ በማዕድን ምርት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በአለም ቀፍ ደረጃ የማዕድን ዋጋ በመቀኑሱ ምክንያትና የዲሞክራሲያዊ አስተዳደሯ ችግር እየበዛበት በመምጣቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቷ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ማሳደር እንደቻለ ኮንትሮል ሪስክ አስነብቧል፡፡

በዚህ አመት ደግሞ አጠቃላይ ይምጣኔ ሃብት እድገቷ ዜሮ ነጥብ አምስት እንደሚሆን የተገመተ ሲሆን የህዝቧ የስራ አጥ ቁጥርም ባልታሰበ መልኩ ከ27 ከመቶ በላይ ደርሷል፡፡

እነዚህ ሁለቱ ሀገራት ከገጠማቸው የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ለመውጣት ረጅም ጊዜያትን የሚወስድባቸው በመሆኑ እና ኢትዮጵያና ኬንያ ደግሞ ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገቡ በመሆናቸው የአህጉሪቱ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤት ሊሆኑ ይችላሉ በማለት ኮንትሮል ሪስክ ይፋ አድርጓል፡፡

ምንጭ፡ ሺንዋ