የአዲስ አበባ ቄራዎች አገልግሎትን ለማዘመን የ7ዐ ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈረመ

መስከረም 4፣2010

የአዲስ አበባ ቄራዎች አገልግሎትን ለማዘመንና ለማስፋፋት  የሚያግዝ የ7ዐ ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ የብድር ስምምነት ከፈረንሳይ የልማት ተራድኦ ድርጅት ጋር ተፈረመ፡፡

በከተማዋ እያደገ የመጣውን የቄራዎች ፍላጎት በጥራትና የአካባቢ ተጽዕኖ በማያስከትል መልኩ የሚያቀርቡ ቄራዎች አናሳ በመሆናቸው አገልግሎቱን ለማዘመንና ለማስፋፋት ስምምነቱ መፈረሙ ተጠቅሷል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚንስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ የብድር ስምምነቱ የአዲስ አበባ ቄራዎች አገልግሎትን ለማዘምንና ለማስፋፋት በተያዘው ፕሮጀክት  ጥራቱን የጠበቀ የእርድ አገልግሎት በማከናወን የስጋ ውጤቶችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዲሁም  ከአካባቢ ተፅዕኖ የፀዳ የቄራ አገልገሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንቲምስ በበኩላቸው እያደገ የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ የቄራዎች ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም የአዳዲስ ቄራዎች ግንባታና ማስፋፋያ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በአዳዲስና በማስፋፊያ ቄራዎች ፕሮጀክት የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት የአሁንና የወደፊት የከተማውን የሥጋ አቅርቦት ፍላጎት ከማርካት ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ትርፋማ እንዲሆን ያስችለዋል ያሉት አምባሳደሩ በሥጋ አቅርቦትና በቆዳ ጥራትም ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለማቅረብ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከ5 ዓመት በኋላ ሲጠናቀቅ በዓመት ከ8ሺ በላይ የቁም እንስሳትን ለእርድ በማቅረብ ከ6ዐ በመቶ በላይ የሚሆነውን የከተማዋን የሥጋ ተጠቃሚዎች ፍላጎት ለማርካት ያግዛል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡