በከባድ ሙስና የተጠረጠሩ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የስራ ሀላፊዎች ክስ ተመሰረተባቸው

መስከረም 3፣2010

የቀድሞው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ፍቃዱ ኃይሌ ከሶስት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር መንግሥት ላይ የ132 ሚሊየን ብር ጉዳት አድርሰዋል በሚል የከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ተመሠረተባቸው፡፡

 

እንደ ክሱ ወንጀሉ ተፈጽሟል የተባለው ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውሀ ልማት ባለው የመንገድ ፕሮጀክት ላይ ነው።

ይህን መንገድ ለመገንባት ኮንትራት የወሰደው ደግሞ በክስ መዝገብ 5ኛ ተራ ቁጥር ላይ የተጠቀስው እስራኤላዊው ተቋራጭ ሚስተር ሚናሼ ሌቪ ነው።

ትድሃር የተሰኘው ይኸው የእስራኤላዊው ኩባንያ ይህንን መንገድ በማጋተቱ ነሐሴ 21 2007 ውሉ ሲቋረጥ ተቋራጭ ከባለስጣን መስሪያ ቤቱ ለማቴርያልና ለተሽከርካሪ ግዥ የወሰደውን ከ132 ሚሊዮን ብር በላይ ቅድመ ክፍያ ባለመመለሱ መንግስት ጉዳት ደርሶበታል ነው ያለው አቃቤ በክሱ።

ተከሳሾች ክሱ ተነቦላቸው ሰምተው የዋስትና ጥያቄ ቢያቀርቡም ከአቃቤ ሕጉ ተቃውሞ በመቅረቡ ግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ የተከሳሾቹን የዋስትና ጥያቄ  ውድቅ በማድረግ በክሱ ላይ መቃወምያ ካላቸው ውጤቱን ለመጠባበቅ ለጥቅምት 9/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ፈለቀ ታደሰን ጨምሮ ስድስት የፋብሪካው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ግለሰቦችም ፋብሪካውን ዘጠና አምስት ሚሊየን ብር አሳጥተውታል በሚል በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ክሱን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን ከ3ዐ ሚሊየን ብር በላይ መንግሥት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል በሚል ወንጀል የተጠረጠ አንድ ግለሰብ በቁጥጥር ሥር አውሎ ፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡

እስክንድር ሰይድ የተባለው ተጠርጣሪ ከሐረር ጅግጅጋ በተገነባው የመንገድ ፕሮጀክት ከሥራ ተቋራጩና ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች ጋር ያልተገባ የጥቅም ትስስር በመፍጠር ከውል ውጪ ከ3ዐ ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ አንዲፈፀም አድርጓል በሚል ወንጀል ነው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡

በተጠርጣሪው ላይ የምርመራ ቡድኑ 14 ቀን የምርመራ ጊዜ ቢጠይቅም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተረኛ ችሎት የተጠርጣሪው ጉዳይ የቀደሞው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ከነበሩት አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል የምርመራ መዝገብ ከተካተቱ 13 ግለሰቦች ጋር ምርመራው ይካሄድ ብሏል፡፡

በእነ አቶ ዘይድ መዝገብ ከሥራ ተቋራጩ አቶ ዛኪር አህመድ ውጭ በሌሎች ላይ ክስ ለመስማት ችሎቱ ለመስከረም 12/2ዐ1ዐ ዓ.ም ቀጠሮ የያዘ ሲሆን ፖሊስ በአቶ ዛኪር ላይ ቀሪ የሰውና የሰነደ ማስረጃዎችን እስከዚሁ ጊዜ እንዲያጠናቅቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡

ዘገባው የሪፖርተራችን ጥላሁን ካሣ ነው፡፡