ሕገውጥ ንግድ አገሪቱ ከወርቅ የውጭ ንግድ የምታገኘውን ገቢ እያሳጣት ነው፦ የማዕድን ሚንስቴር

ጳጉሜ 3፣2009

ሕገወጥ ንግድ አገሪቱ ከወርቅ የውጭ ንግድ የምታገኘውን ገቢ እያሳጣት መሆኑን የኢፌዲሪ የማዕድን ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

በሚንስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ባጫ ፋጁ በተለይ ለኢቢሲ እንደተናገሩት በ2009 በጀት ዓመት ከወርቅና ከሌሎች የከበሩ ማዕድናት 230 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በውጭ ንግድ  ተገኝቷል፡፡

ሆኖም ገቢው ከእቅዱ አኳያ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም በክልሎች ያለውን የወርቅ ግብይት ሂደት የሚደግፍ ምቹ አደረጃጀትና የተሟላ የሰለጠ የሰው ሀይል እጥረት በመኖሩ መሆኑን ሀላፊው ጠቅሰዋል፡፡

እንዲሁም ክልል በሚገኙ ወርቅ አምራቾችና በህጋዊ መንገድ ወርቅ በሚረከበው ንግድ ባንክ መካከል ረጅም የግብይት ሰንሰለት በመኖሩ ምርቱ በሕገወጥ ንግድ ተዋኒያኖች እጅ ይወድቃል ብለዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ በወርቅ አምራቾችና አቅራቢዎች መካከል ያለውን እርቀት በማሳጠር የግብይት ሂደቱን ለማቀላጠፍ በ5 ክልሎች 5 የወርቅ መገበያያ ማዕከላት መገንባቱን ሀላፊው አመልክተዋል፡፡

ማዕከላቱም በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብና በቤንሻንጉል ጉሙዝ እንደተገነቡም ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በፊት የወርቅ አምራቾች ምርታቸውን በእርቅት በሚገኙ ማዕከላት ስለሚያቀርቡ በሂደቱ ለእንግልት ከመዳረግ በተጨማሪ ምርታቸውን ለሕገወጥ ገበያ ለማቅረብ በር የሚከፍት ስለነበረ ሀገሪቷ ከውጭ ንግድ ማግኘት የሚገባትን ገቢ አሳጥቷታል ብለዋል አቶ ባጫ፡፡  

አሁን ግን በወርቅ አምራቾች አቅራቢያ የተገነቡት ማዕከላት ይህን ችግር በማቃለል ሻጭና ገዢን በቅርበት ለማገናኘት ፋይዳቸው የጎላ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ይህ አሰራር የዘርፉ ግብይት በግልጽ እንዲከወንና መረጃዎች በስርዓት እንዲያዙ ያግዛሉ ነው የተባለው፡፡

በበጀት ዓመቱ ከተመረተው 6 ቶን ገደማ ወርቅ ውስጥ 2 ቶን ገደማ በባህላዊ የማዕድን አምራቾች የተመረተ ሲሆን ቀሪው ደግሞ በሜድሮክ ኩባንያ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በቀጣይ ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን የውጪ ገቢን ለማሳደግ ከወርቅ በተጨማሪ ሌሎች የከበሩ ማዕድናትን በዓይነትና በብዛት ለማልማት እንደሚሰራም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አመልክቷል፡፡

በአሁን ወቅት በሀገሪቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚልቁ ዜጎች በባህላዊ የወርቅ ማዕድን ምርት ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡

በወርቅ ግብይት ህገ-ወጥ ንግድን ለመቀነስም ወርቅ አምራቶች ለንግድ ባንክ ከ150 ግራም በታች ወርቅ እንዲያቀርቡ ለማስቻል እየተሰራም እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

ሪፖርተር፦ ሰለሞን አብርሃ