ኢትጵጵያ ድርቅን ለመቋቋምና ልማትን ለማፋጠን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች- ም/ጠ/ሚ/ር ደመቀ መኮንን

ነሃሴ 29፤2009

ኢትዮጵያ በየጊዜው የሚከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም እና በሀገሪቱ ልማትን በዘላቂነት ለማስቀጠል ከተለያዩ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር መስራትዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአለም አቀፉ የግብርና ልማት ፈንድ / IFAD / ቦርድ አባላት ጋር እንዲሁም መቀመጫቸውን በጣሊያን ሮም ያደረጉት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምግብ እና እርሻ ድርጅት /FAO/ እና የአለም የምግብ ፕሮግራምን /WFP/ ተወካዮችን ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

የአለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ /Ifad/ ፕሬዝዳንት ጊልበርት ሆንግቦ ቦርዱ በኢትዮጵያ ሶማሌ እና በትግራይ ክልሎች በመገኘት ድርጅቱ እያከናወነ ያለውን ተግባር እና አፈፃፀም መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት ቆይታም በቀጣይ ኢትዮጵያ ለዘላቂ ልማትዋ እያከናወነች ያለውን ሥራ ለመደገፍ በር የከፈተ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ድርጅታቸው በሃገሪቱ በተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃቸው ቦታዎች ላይ የውሃ እጥረት እንዳይኖር የመስኖ ልማትን ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡