አዲስ የማጅራት ገትር በሽታ የምርመራ ስልት ተግባራዊ ሊደረግ ነው

ነሀሴ24 ፤2009

በገዳይነቱ የሚታወቀውና በተለምዶ የማጅራት ገትር በሽታ ተብሎ የሚጠራውን ሜነንጃይትስ ፈጣን በሆነ መልኩ በመመርመር የሰውልጆችን ህይወተ ሊታደግ ይችላል የተባለለት የምርመራ ስልት በአየርላንድ በተግባር ላይ ሊውል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ማነጃይትስ በሰአታት ውስጥ የሰውልጅ ህይወትን የመቅጠፍ አቅም ቢኖረውም ከዚህ ቀደም በስራ ላይ የነበረው ምርመራ እስከ 2 ቀናት ይወስድ ነበር፡፡

በተግባር ላይ ለመዋል የተዘጋጀው የምርመራ ስልት ከ60 ደቂቃዎች ባነሰ ጊዜ ውስጥ አንድ ሰው በበሽታው መያዝ አለመያዙን ለማረጋገጥ ያስችላል ተብሏል፡፡

ይህም ሀኪሞች በበሽታው የተያዘውን ሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ በመለየት ትክክለኛውን ህክምና በሽተኛው እንዲያገኝ ያስችላል፡፡

የማጅራት ገትር በሽታ በድንገት የሚከሰትና የአንጎልንና የህብለሰረሰር ሽፋን የሆነውን ስስ አካልን በማስቆጣት ከፍተኛ የህመም ስሜት የሚያስከትል ተላላፊ በሽታ ነው፡፡

በአገራችን በአብዛኛው በሽታው በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት ሲሆን ለዚህ በሽታ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ስያሜዎች ይሰጠዋል፤ በስፋት የሚታወቁት ስያሜዎቹ ግን ማንጅራት ገትር፣ የጋንጃ በሽታና ሞኝ ባገኝ የሚባሉት ናቸው፡፡

በሽታው በማንኛውም እድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ላይ ሊከሰት የሚል ሲሆን በተለይ ግን ህፃናትና ወጣቶች ይበልጥ በበሽታው ተጠቂ ናቸው፡፡

በሃገራችን በሽታው አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በጣም ሞቃታማ፣ ደረቅና ነፋሻማ የአየር ጠባይ በሚታይበት ጊዜ ሲሆን በማጅራት ገትር ወረርሸኝ የሚታወቁት ወራት በተለይ ጥር፣ የካቲት፣ መጋቢት፣ ሚየዚያና ግንቦት ናቸው፡፡

ምንጭ፡- ቢቢሲ