የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንግስት አስታወቀ

ነሐሴ 05፣2009

በአመለካከት ለውጥ የታገዘ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መንግስት አስታወቀ።

ሰሞኑን የመንግስትና የህዝብን ሃብትና ንብረት መዝብረዋል በሚል የተጠረጠሩ ባለስልጣናትና የተለያዩ ግለሰቦች በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር እየዋሉ መሆኑን ነው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ ላይ የጠቀሰው፡፡

ጽህፈት ቤቱ የሙስና ተግባራትን በዝርዝር በማጥናትና በማጣራት ረዘም ያለ ሂደት እንዲያልፍ መደረጉም የዜጐች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዳይሸራረፉ የተደረገውን ጥንቃቄ አመላካች ነው ብሏል በመግለጫው፡፡

ጽሕፈት ቤቱ የሙስና ወንጀሎችን በማጋለጥ የህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያለው መግለጫው የመገናኛ ብዙሃንም የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባራትን በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፈው በማጋለጥ ረገድ ገንቢ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሷል፡፡