ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትፈልግ ገለጸች

ነሀሴ 4 ፤2009

ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጀ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት አስታወቀች፡፡

የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይና ትብብር ሚኒስትሯ ሎዊስ ሙስኮዋል ከፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ያመጡትን መልዕክት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትሯ በቅርቡ ፖል ካጋሜ ለ7ዓመታት ሀገሪቱን ለመምራት የሚያስችላቸውን ድምፅ ማግኘታቸውን ተከትሎ በቀጣይ ጊዜያት ሩዋንዳ ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚና በመሠረተ ልማት ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ሩዋንዳ ዝግጁ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ረዳት አምባሳደር እውነቱ ብላታ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሩዋንዳ ያላቸው ግንኙነት እየተጠናከረ መጥቷል ለዚህም በቅርቡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኪጋሊ መከፈቱ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

አምባሳደር እውነቱ ሁለቱ ሀገራት በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም በኬንያ ምርጫ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡