እርስዎ ያለ አብራሪ በሚንቀሳቀስ አውሮፕላን ላይ እንዲጓዙ ቢጠየቁ ምርጫዎ ምን ይሆናል?

ነሀሴ3 ፣2009

ያለ አብራሪ/ፓይለት/ የማይሰራው የመንገደኞች አውሮፕላን ጥቅም ላይ ሊውል ነው፡፡

በአለማችን በየጊዜው የሰዎችን ምቾት የሚጠብቁ ፈር ቀዳጅ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ይፋ እየተደረጉ ይገኛል፡፡

ለዚህም እንደ ማሳያ ያለአሽከርካሪ የሚነዳ ዘመን አፈራሽ መኪና በጥቂት የአሜሪካ ከተሞች በከፊል ስራ ላይ ሲውል በለንደን እንግሊዝ ደግሞ በሙከራ ላይ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡

በአሁን ወቅት ደግሞ በአውሮፕላን አብራሪ የማይሰራ የመንገደኞች አውሮፕላን እ.ኤ.አ በ2018 በቦይንግ  አውሮፕላን አምራች ኩባንያ ለሙከራ ሊበቃ እንደሆነ ተነግሯል፡፡  

አውሮፕላኑ የተሳካ ሙከራ አድርጎ ስራ ሲጀመር ከርቀት ሰዎች እየተቆጣጠሩት አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡

የአውሮፕላን ትራንስፖርት በአለም ከሚገኙ የትራንስፖርት አይነቶች ደህንነቱ በእጅጉ የተጠበቀ እንደሆነ ይነገራል፡፡

ከዚህ ውስጥ ደግሞ በአብራሪ የማይሰራ አውሮፕላን ከመደበኛ የመንገደኞች አውሮፕላን ይልቅ ደህንነቱ የተጠበቀ እንደሆነ የሲውዘርላንድ የፋይናንስ አገልግሎት ኩባንያ ባካሄደው ጥናት አመልክቷል፡፡

ሆኖም ኩባንያው በተለያዩ እድሜ የሚገኙ 8 ሺህ ሰዎች አዲሱ አውሮፕላንን ምርጫቸው ያደርጉ እንዲሆን ባጠናው ጥናት መሰረት 54 በመቶ የሚሆኑት በአውሮፕላኑ እንደማይሳፈሩ ተናግረዋል፡፡  

ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ እድሜያቸው ከ45 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች አዲሱን አውሮፕላን በመጠቀም ረገድ በአመዛኙ እንደማይስማሙ አመልክተዋል፡፡

በጥናቱም 17 በመቶ የሚሆኑት በአብዛኛው ወጣቶች በአውሮፕላኑ እንደሚሳፈሩ ፍላጎታቸውን አሳይተዋል ተብሏል፡፡

ከ70 እስከ 80 በመቶ የሚሆነው የአውሮፕላን አደጋዎች በሰዎች በተለይም በአውሮፕላን አብራሪዎች እንደሚከሰት ተመልክቷል፡፡

ይሁንና አዲሱ አውሮፕላን ይህን ችግር በመቀልበስ ረገድ አይነተኛ መፍትሄ ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡

አውሮፕላን ያለ አብራሪ በተጨማሪም እራሱን ችሎ በኮምፒውተር መቆጣጠሪያ መሳሪያ በመታገዝ መደበኛ በረራውን እንደሚከውን የዘርፉ ባለሞያዎች ይገልፃሉ፡፡ 

በዚህም ወቅት የኮምፒውተር ስርዓቱ የሚጠበቅበትን ስራ ሳይከውን ሲቀር አልያም ሲበላሽ የአውሮፕላን ፓይለቶቹና ሰራተኞቹ ችግሩን ለማስተካከል ጣልቃ ይገባሉም ነው የሚባለው፡፡

ይሁን እንጂ አብራሪ አልባ የሚሰራ አውሮፕላን ስራ ላይ ከዋለ ግን ይህን ችግር ለማስተካከል አዳጋች ስለሚሆን አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል ስቲቭ ላንዴልስ የተባለ የአየር ጉዞ ደህንነት ባለሞያ ተናግሯል፡፡

ምንጭ፦ቢቢሲ