ጋና ወደ ጠፈር ያመጠቀቻት የመጀመሪያዋ ሳተላይት በህዋ ውሰጥ ሙከራዋን ጀመረች

ነሐሴ 1፣ 2009

ጋና ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጠፈር ያመጠቀችው ሳተላይት በመሬት ምህዋር ላይ በመዞር የሙከራ ተልዕኮዋን ማከናወን ጀመረች፡፡

በጋና የመሀንዲሶች ቡድን እንደተገነባች የተነገራላት ሳተላይት ባለፈው ሰኔ ወር ነበር አሜሪካ ከሚገኘው የጠፈር መንኮራኩር ማምጠቂያ ማዕከል ናሳ፣ ተነስታ አለም አቀፍ የጠፈር ምርምር ጣቢያን የተቀላቀለችው፡፡  

ጠፈር ከሚገኘው ከዚህ ምርምር ማዕከል ደግሞ ከሐምሌ ጀምሮ ሳተላይቷ መሬትን መዞር እንደጀመረች በአሜሪካ የጠፈር ምርምር ተቋም/ናሳ/ የሚሰሩት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ዳሞህ ተናግረዋል፡፡ 

ሳተላይቷ ሁለት ተልኮ እንዳላት የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ በተገጠመላት የምስል ማሳያ/ካሜራ/ የጋናን የባህር ዳርቻ አልያም ድንበር ለመከታተል ይረዳል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ትምህርት ዘርፍ ውስጥ የሳተላይት ቴክኖሎጂን ከሁለተኛ ደረጃ ስርዓተ ትምህርት ጋር ለማቀናጀት ያግዛል ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ፡፡  

በጋና ‹‹ኦል ኔሽንስ ዮኒቨርስቲ›› በተመራማሪዎች የተገነባው ሳተላይትም በቀጣይ ለዩኒቨርስቲው የህዋ ምርምርና የቴክኖሎጂ ቤተሙከራ መረጃዎችን ያቀብላል ተብሎ ይጠበቃል ተብሏል፡፡

በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ እና ሌሎች በርካታ ሀገሮች የጠፈር ምርምር ተቋም እንዳላቸው ያስነበበው ዘገባው ፣ የጋና ጥረት የተሻለ መነቃቃትን ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ምንጭ፦ቴክ ክራንች ድረ-ገጽ