ለአቶ ክፍሌ ወዳጆ እና አቶ አማረ አረጋዊ እውቅና ተሰጣቸው

ሐምሌ 07፤2009

አቶ ክፍሌ ወዳጆ በኢትዮጵያ ሀሳብ የመግለፅ፣ የመናገርና የመፃፍ ነፃነት እንዲከበር በብርቱ በመታገል ላበረከቱት አስተዋፅኦ ነው እውቅናው የተሰጣቸው፡፡

አቶ ክፍሌ ወዳጆ በ1987 ዓ.ም የፀደቀውን ሕገመንግስት ያረቀቀውንና ያፀደቀውን ኮሚሽን የመሩ ሲሆን የሚድያ አስፈላጊነትን በማሳመን ውይይት ላይ ንቁ ተሳትፎም አድርገዋል፡፡

አቶ አማረ አረጋዊም የመንግስት መገናኛ ብዙሀንን በመሩባቸው ወቅቶች ባስመዘገቧቸው ውጤቶችና የሪፖርተር ጋዜጦችና መፅሄቶችን በማቋቋም ለመገናኛ ብዙሀን እድገት ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

አቶ አማረ አረጋዊ የአፍሪካ ቀንድ ፕሬስ ተቋምንና በቅርቡ ስራ የሚጀምረውን የአፍሪካ ህዳሴ ቴሌቪዥንን እንደሚመሩም ተገልጿል፡፡

በእውቅና አሰጣጡ ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ መገናኛ ብዙሀን በአገሪቱ እድገት ላይ ውጤታ ስራዎች እንዲሰሩ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን ሁሉም አካላት ሊሳተፉ ይገባዋል ብለዋል፡፡

ተአማኒና ተፅዕኖ ፈጣሪ መገናኛ ብዙሃንን ለመገንባት ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቅድመ ምርመራ ሳንሱር በአዋጅ ከቀረና የግል ፕሬስ ፍቃድ ካገኘ 25 አመታት ተቆጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢዮብ ሞገስ