በብሔራዊ ፓርኮች የዱር እንስሳቶች ቁጥር እየተበራከተ ነው፦ ባለስልጣኑ

ሐምሌ 07፣2009

በአገሪቱ ባሉ ብሔራዊ ፓርኮች የዱር እንስሳቶች ቁጥር በየጊዜው እየተበራከቱ መሆኑን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ገለፀ::

ለእንስሳቱ ቁጥር መጨመር በፓርኮቹ ላይ በቂ ጥበቃና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመሰራቱ መሆኑንም ባለስልጣኑ አመልክቷል።

በባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ በተለይ ለኢቢሲ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት ዘርፉን ለማልማትና ለመጠበቅ እየተሰራ ባለው ስራ ሰባት ፓርኮች ህጋዊ ሰውነት እንዲኖራቸው ተደርጓል፡፡

በበጀት ዓመቱ በሀገሪቱ በተከሰተ ሁከትና ብጥብጥ ምክንያት በመንፈቅ ዓመቱ ከብሔራዊ ፓርኮች የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው ባለፉት ወራት በሀገሪቱ በተፈጠረው መረጋጋትና ሰላም በፓርኮቹ ያለው የቱሪዝም ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ፓርኮች በሰዎች የመኖሪያ ቤቶች፣ በግብርና ማሳ ስራዎችና በከብት ግጦሽ እየተወረሩ በመሆኑ አደጋ ውስጥ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ በፓርኮቹ ውስጥ የሚኖሩ ማህበረሰቦች አካባቢውን እንዲጠብቁና እንዲንከባከቡ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በፊንቂሌ የቆርኪዎች መጠለያ ላይ የቆርኪዎች ቁጥር ከዚህ በፊት ከነበረው 70 አሁን ላይ ወደ 900 ሲደርስ በሰሜን ተራሮች ደግሞ የዋሊያዎች ቁጥር እንደዚሁ ጨምሯል ብለዋል፡፡   

ሆኖም የባቢሌ ብሔራዊ ፓርክ በአካባቢው ህብረተሰብ ጉዳት እየደረሰበት ስለሆነ በቀጣይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራው እንደሚጠናከር አመልክተዋል፡፡

በፓርኮቹ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከአካባቢው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን የማሳደግና በፓርኮች ዙሪያ በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፓርኮቹ ለቱሪዝም መስህብ ምቹ እንዲሆኑ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች በተለይም የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን መገንባትና የውሃ አቅርቦትን የሟሟላት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

24 ብሔራዊ ፓርኮችና 2 የዱር እንስሳት መጠለያዎችን በሀገሪቱ እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሪፖርተር፦ሰለሞን አብርሃ