የአዲስ አበባ ምክር ቤት 1ዐኛውን የአዲስ አበባ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን አፀደቀ

ሐምሌ 06፣2009

የአዲስ አበባ ምክር ቤት 1ዐኛውን የአዲስ አበባ ከተማ መዋቅራዊ ፕላን አፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ እያካሄደ ባለው የ4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 3ኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው  የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን ያፀደቀው፡፡

የከተማዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ለምክር ቤቱ  የተቀናጀ የጋራ መሪ ፕላኑ ከተሰረዘ  በኃላ የከተማ አስተዳደሩ የራሱን መሪ ፕላን ማዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

መዋቅራዊ ፕላኑ የከተማዋን እድገት ወደ ላይ ብቻ  የተወሰነ በማድረግ ውስን የሆነውን መሬት በአግባቡ ለመጠቀም እድል የሚፈጥር ሆኖ መዘጋጀቱን ለምክር ቤቱ አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባና ኦሮሚያ መካከል ያለውን ወሰን ለመለየት በሁለቱ አካላት መካል ጥናት የሚያካሂድ ኮሚቴ መዋቀሩንም አመልክተዋል፡፡ከጥናቱ በኃላም የወሰኑ ጉዳይ በግልፅ መፍትሄ እንደሚያገኝ ከንቲባ ድሪባ ተናግረዋል፡፡

ምክር ቤቱ በ10ኛው የአዲስ አበባ መዋቅራዊ  ፕላን ዙሪያ ሀሳብና አስተያየት ከሰጠ በኋላ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎ አፅድቆታል፡፡

ምንጭ ፡‑ የአዲስ አበባ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት