ኢጋድ ለሁሉም የቀጠናው ማህበረሰብ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት እንዲቀርብ ጠየቀ

ሐምሌ 06፣2009

የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግስታት /ኢጋድ/ ለሁሉም የቀጠናው ማህበረሰብ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎትን ማቅረብ እንደሚገባ አስታወቀ፡፡

የተለያዩ የመረጃ አማራጮችን መሰረት በማድረግ ድንበር በሚጋሩ የቀጠናው ሀገራት ውስጥ ተላላፊና ተሻጋሪ የሆኑ በሽታዎችን መከላከል በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ በአዲስ አበባ ውይይት ተካሒዷል፡፡

በጉባኤው የኢጋድ ዋና ፀሀፊ ተወካይ ወ/ሮ ፈቲያ አልዋን መረጃን መሰረት ያደረጉ የጤና ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት ፈታኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሰራት ይገባል ብለዋል፡፡

በዋናነት በእናቶችና ህፃናት ሞት እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ተላላፊ በሽታዎች መቀነስም በመድረኩ ትኩረት ተሰጥቷቸው ምክክር ተደርጎባቸዋል፡፡

በቀጠናው  የተሰበሰቡ መረጃዎች የኢጋድ ሃገራት ጥብቅ ክትትል የተደረገባቸው ፖሊሲዎችና ኘሮግራሞች ፈጥነው ወደ ስራ መግባት እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳዩ መሆናቸውን ተወካይዋ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኢፌዲሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ኘሮፌሰር ይፍሩ ብርሃነ እንዳሉት የቀጠናው ሀገራት በተለይ ድንበር ተሻጋሪ በሆኑ የጤና ጉዳዮች ላይ በቅርበት በመምከር የዜጐቻቸውን ጤና ማረጋገጥ ይገባቸዋል ፡፡

መንግስት ከሀገራቱ ጋር በቅርበት ለመስራት የጤና ነክ መረጃዎችን እየተለዋወጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምንጭ ፡‑ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር